ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 4:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ስለዚህ ሀታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ከተማዪቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ።

7. መርዶክዮስ የደረሰበትን ነገር ሁሉ፣ እንዲሁም ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማግባት ቃል የገባውን የገንዘብ ልክ ጭምር ነገረው።

8. አይሁድን ለማጥፋት በሱሳ የወጣውን የዋናውን ዐዋጅ ቅጅም ለአስቴር እንዲያሳያትና በዝርዝር እንዲያስረዳት ሰጠው፤ ወደ ንጉሡም ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝቧ ምሕረት እንድትጠይቅና እንድትማልድ አጥብቆ ይነግራት ዘንድ አሳሰበው።

9. ሀታክም ተመልሶ መርዶክዮስ የነገረውን ሁሉ ለአስቴር አስታወቃት።

10. እርሷም ለመርዶክዮስ እንዲህ እንዲለው ነገረችው፤

11. “የንጉሡ ባሮችና በንጉሡ አውራጃዎች የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፣ ማንም ሰው ሳይጠራ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚገባ፣ ንጉሡ አንድ ሕግ ብቻ እንዳለው ያውቃል፤ ይኸውም እንዲህ ያደረገው ሰው ይገደላል፤ አንድ ሰው ከእንዲህ ዐይነቱ ሞት የሚተርፈው፣ ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ሲዘረጋለት ብቻ ነው። እኔ ግን ወደ ንጉሡ ዘንድ እንድገባ ከተጠራሁ ከሠላሳ ቀን በላይ ሆነ።”

12. የአስቴር ቃል ለመርዶክዮስ በተነገረው ጊዜ፣

13. ይህን መልስ ላከባት፤ “አንቺ በንጉሥ ቤት በመሆንሽ ብቻ ሌላው የአይሁድ ሕዝብ ሲጠፋ አንቺ የምትተርፊ እንዳይ መስልሽ፤

14. በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትዪ፣ ለአይሁድ ርዳታና ትድግና ከሌላ ስፍራ ይመጣላቸዋል፤ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ አንቺ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?”

15. ከዚያም አስቴር ለመርዶክዮስ ይህን መልስ ላከችበት፤

16. “ሂድና በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ በአንድነት ሰብስብ፤ ስለ እኔም ጹሙልኝ፤ ቀንም ይሁን ሌሊት ለሦስት ቀን አትብሉ፤ አትጠጡም። እኔና ደንገጡሮቼም እናንተ እንደምታደርጉት ሁሉ እንጾማለን፤ ይህ ከተፈጸመ በኋላ ግን ነገሩ ምንም እንኳ ከሕግ ውጭ ቢሆንም፣ ወደ ንጉሡ ዘንድ እሄዳለሁ፤ ከጠፋሁም ልጥፋ።”

17. ስለዚህ መርዶክዮስ ሄደ፤ የአስቴርንም ትእዛዝ ሁሉ ፈጸመ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 4