ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 9:25-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. የተመሸጉ ከተሞቻቸውንና የሰባውን ምድር ያዙ፤ በመልካም ነገር ሁሉ የተሞሉ ቤቶቻቸውን፣ የተቈፈሩ የውሃ ጒድጓዶቻቸውን፣ የወይን ተክላቸውን፣ የወይራ ዛፎቻቸውንና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የፍሬ ዛፎች ያዙ። እስኪጠግቡ በሉ፤ ወፈሩም፤ በታላቅ በጎነትህም ደስ ተሰኙ።

26. “ነገር ግን እንቢተኞች ሆኑ፤ ዐመፁብህም፤ ሕግህንም አሽቀንጥረው ጣሉ፤ ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩት ነቢያትህን ገደሉ፤ አስጸያፊ የስድብ ቃልም ተናገሩ።

27. ስለዚህ ላስጨነቋቸው ጠላቶቻቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ አንተ ጮኹ፤ አንተም ከሰማይ ሰማሃቸው፤ ከርኅራኄህም ብዛት የተነሣ ከጠላቶቻቸው እጅ የሚያድኗቸውን ታዳጊዎች ሰጠሃቸው።

28. “ነገር ግን ዕረፍት ባገኙ ጊዜ፣ በፊትህ ክፉውን ነገር እንደ ገና ፈጸሙ፤ ከዚያም ይገዟቸው ዘንድ በጠላቶቻቸው እጅ ጣልሃቸው፤ እንደ ገና ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ፣ ከሰማይ ሰማህ፤ በርኅራኄህም በየጊዜው ታደግሃቸው።

29. “ወደ ሕግህ እንዲመለሱ አስጠነቀቅሃቸው፤ እነርሱ ግን እብሪተኞች ሆኑ። ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም፤ አንድ ሰው ቢፈጽማቸው በሕይወት የሚኖርባቸውን ሥርዐቶችህን ተላለፉ። እምቢተኞች ሆነው ጀርባቸውን አዞሩብህ፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ መስማትም አልፈለጉም።

30. ብዙ ዘመን ታገሥሃቸው፤ በነቢያትህ አማካይነት በመንፈስህ አስጠነቀቅሃቸው። ነገር ግን አላደመጡህም፤ ከዚህም የተነሣ ጎረቤቶቻቸው ለሆኑ አሕዛብ አሳልፈህ ሰጠሃቸው።

31. አንተ ግን ቸርና መሓሪ አምላክ ነህና ከምሕረትህ ብዛት የተነሣ፣ ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፤ አልተውሃቸውምም።

32. “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ ቃል ኪዳንህንና ዘላለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ ታላቅ፣ ኀያልና የተፈራህ አምላክ ሆይ፤ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችንና በመሪዎቻችን፣ በካህናታችንና በነቢያታችን፣ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ የደረሰው ይህ ሁሉ መከራ በፊትህ እንደ ቀላል ነገር አይታይ።

33. በደረሰብን ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛ በደለኞች ነን፤ አንተ ግን ትክክለኛውን አደረግህ።

34. ነገሥታታችን፣ መሪዎቻችን፣ ካህናታችንና አባቶቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ ትእዛዞችህን ወይም የሰጠሃቸውን ማስጠንቀቂያዎች አልሰሙም።

35. በገዛ መንግሥታቸው፣ በሰጠሃቸው ታላቅ በጎነትህና በፊታቸውም ባዘጋጀህላቸው ሰፊና ለም ምድር እንኳ፣ አንተን አላገለገሉም፤ ከክፉ መንገዳቸውም አልተመለሱም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 9