ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 13:15-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. በእነዚያ ቀናት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጭመቂያ የሚረግጡ፣ እህል የሚያስገቡና፣ የወይን ጠጅ፣ የወይን ዘለላ፣ የበለስና ሌሎችን የጭነት ዐይነቶች ሁሉ በአህያ ላይ የሚጭኑ ሰዎች አየሁ፤ ይህን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ያስገቡ የነበረው በሰንበት ቀን ነበረ። ስለዚህ በዚያን ቀን ምግብ እንዳይሸጡ ከለከልኋቸው።

16. በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የጢሮስ ሰዎችም ዓሣና ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ በሰንበት ቀን እያመጡ ለይሁዳ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ይሸጡ ነበር።

17. እኔም የይሁዳን መኳንንት በመገሠጽ እንዲህ አልኋቸው፤ “ሰንበትን በማርከስ ይህ የምትፈጽሙት ክፉ ድርጊት ምንድን ነው?

18. የቀድሞ አባቶቻችሁ ያደረጉት ይህንኑ አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ሁሉ ጥፋት በእኛና በዚች ከተማ ላይ ያመጣው በዚሁ በደላችን አይደለምን? አሁንም እናንተ ሰንበትን በማርከስ የባሰ መከራ በእስራኤል ላይ ታመጣላችሁ።”

19. በሰንበት ዋዜማ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ የምሽቱ ጥላ ማረፍ ሲጀምር በሮቹ እንዲዘጉና፣ ሰንበት እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ፤ በሰንበት ቀን ጭነት እንዳይገባም ከራሴ ሰዎች አንዳንዶቹን በየበሩ ላይ አቆምሁ።

20. የልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎችና ቸርቻሪዎች ከኢየሩሳሌም ውጭ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ አድረዋል።

21. እኔ ግን፣ “ከቅጥሩ ውጭ የምታድሩት ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ዳግመኛ ብታደርጉ እጄን አነሣባችኋለሁ” ስል አስጠነቀቅኋቸው፤ እነርሱም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሰንበት ቀን አልመጡም።

22. ከዚያም ሌዋውያኑ ራሳቸውን እንዲያነጹ፣ ሄደውም የቅጥሩን በር እንዲጠብቁና የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ አዘዝኋቸው።አምላኬ ሆይ፤ ስለዚህም ደግሞ አስበኝ፤ እንደ ታላቅ ፍቅርህም ብዛት ምሕረት አድርግልኝ።

23. በእነዚያም ቀናት የአሽዶድን፣ የአሞንንና የሞዓብን ሴቶች ያገቡ አይሁድ አገኘሁ።

24. ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ የአሽዶድን፣ ወይም ከሌሎቹ ሕዝቦች የአንዱን ቋንቋ እንጂ የአይሁድን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር።

25. እኔም ገሠጽኋቸው፤ ርግማንም አወረድሁባቸው። አንዳንዶቹን መታኋቸው፤ ጠጒራቸውንም ነጨሁ። በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ስል አማልኋቸው፤ “ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ።

26. የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ኀጢአት የሠራው እንዲህ ከመሰለው ጋብቻ የተነሣ አይደለምን? በብዙ መንግሥታት መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፤ በአምላኩም የተወደደ ነበረ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ አደረገው። ነገር ግን ባዕዳን ሴቶች ወደ ኀጢአት መሩት።

27. እናንተም ደግሞ ባዕዳን ሴቶችን በማግባት ይህን የመሰለ ታላቅ በደል እንደምትፈጽሙና ለአምላካችንም ታማኞች እንዳልሆናችሁ መስማት ይገባናልን?

28. ከሊቀ ካህኑ ከኤልያሴብ ልጅ ከዮአዳ ልጆች አንዱ የሖሮናዊው የሰንባላጥ አማች ነበረ፤ እኔም ከአጠገቤ አባረርሁት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 13