ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 12:30-42 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. ካህናቱና ሌዋውያኑ በሥርዐቱ መሠረት ራሳቸውን ካነጹ በኋላ፣ ሕዝቡን፣ ቅጥሩና በሮቹን አነጹ።

31. እኔም የይሁዳን መሪዎች በቅጥሩ ግንብ አናት ላይ እንዲወጡ አደረግሁ፤ ደግሞም ምስጋና እንዲያቀርቡ ሁለት ታላላቅ የመዘምራን ቡድን መደብሁ። አንዱ በቅጥሩ ግንብ አናት በስተ ቀኝ በኩል “ቈሻሻ መጣያ በር” ወደሚባለው ሄደ።

32. እነዚህንም ሆሻያና ከይሁዳ አለቆች እኩሌቶቹ ተከተሏቸው፤

33. የተከተሏቸውም ከዓዛርያስ፣ ከዕዝራ፣ ከሜሱላም፣

34. ከይሁዳ፣ ከብንያም፣ ከሸማያ፣ ከኤርምያስና፣

35. እንዲሁም መለከት ከያዙ ጥቂት ካህናትና ከአሳፍ ልጅ፣ ከዘኩር ልጅ፣ ከሚካያ ልጅ ከመታንያ ልጅ፣ ከሸማያ ልጅ፣ ከዮናታን ልጅ፣ ከዘካርያስ ጋር ነበር።

36. ወንድሞቹ ሸማያ፣ ኤዝርኤል፣ ሚላላይ፣ ጊላላይ፣ መዓይ፣ ናትናኤል፣ ይሁዳና አናኒም የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ባዘዘው መሠረት የዜማ መሣሪያዎቹን ይዘው ሄዱ፤ ሰልፉን የሚመራውም ጸሓፊው ዕዝራ ነበረ።

37. “ከምንጭ በር” ተነሥተው በቀጥታ ወደ “ዳዊት ከተማ” ደረጃዎች ወጡ፤ ከዚያም በቅጥሩ መውጫ በኩል አድርገው ከዳዊት ቤት በላይ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ወደ “ውሃ በር” ሄዱ።

38. ሁለተኛው የመዘምራን ቡድን በስተ ግራ በኩል ሄደ፤ እኔም ከከፊሉ ሕዝብ ጋር ሆኜ በቅጥሩ ግንብ ላይ፣ የእቶኑን ግንብ በማለፍ እስከ ሰፊው ቅጥር ተከተልኋቸው፤

39. ከዚያም ከኤፍሬም በር በላይ፣ በአሮጌ በር፣ በዓሣ በር፣ በሐናንኤል ግንብ፣ በመቶዎቹ ግንብ አልፌ እስከ “በጎች በር” ድረስ ተከተልኋቸው። እነርሱም “በዘበኞች በር” አጠገብ ሲደርሱ ቆሙ።

40. ቀጥሎም ምስጋና ያቀረቡት ሁለቱ የመዘምራን ቡድኖች፣ በእግዚአብሔር ቤት ቦታቸውን ያዙ፤ እኔም ከግማሾቹ ሹማምት ጋር ቦታዬን ያዝሁ፤

41. እንደዚሁም ካህናቱ ኤልያቄም፣ መዕሤያ፣ ሚንያሚን፣ ሚካያ፣ ኤልዮዔናይ፣ ዘካርያስና ሐናንያ መለከታቸውን ይዘው፣

42. መዕሤያ፣ ሸማያ፣ አልዓዛር፣ ኦዚ፣ ይሆሐናን፣ መልክያ፣ ኤላምና ኤጽር ቦታቸውን ያዙ፤ መዘምራኑ በይዝረሕያ መሪነት ዘመሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 12