ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 12:22-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. በኤሊያሴብ፣ በዮአዳ፣ በዮሐናንና በያዱአ ዘመን የሌዋውያኑ ቤተ ሰብ አለቆችና ካህናቱ፣ በፋርሳዊው በዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ተመዝግበው ነበር።

23. ከሌዋውያን ዘሮች መካከል እስከ ኤሊያሴብ ልጅ እስከ ዮሐናን ድረስ ያሉት የየቤተ ሰቡ ኀላፊዎች በታሪክ መጽሐፍ ተመዝግበው ነበር።

24. የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሸብያ፣ ሰራብያ፣ የቀድምኤል ልጅ ኢያሱ ነበሩ፤ እነርሱም ከወንድሞቻቸው ፊት ለፊት ሆነው የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት በሰጠው መመሪያ መሠረት እየተቀባበሉ ውዳሴና ምስጋና ያቀርቡ ነበር።

25. በቅጥሩ በሮች አጠገብ ያሉትን ዕቃ ቤቶች የሚጠብቁት ዘቦች ደግሞ መታንያ፣ በቅቡቅያ፣ አብድዩ፣ ሜሱላም፣ ጤልሞንና ዓቁብ ነበሩ።

26. እነዚህም በኢዮሴዴቅ ልጅ፣ በኢያሱ ልጅ በዮአቂም፣ በአገረገዢ በነህምያ፣ በካህኑና በጸሓፊው በዕዝራ ዘመን አገለገሉ።

27. የኢየሩሳሌም ቅጥር ሲመረቅ ሌዋውያኑ በምስጋና መዝሙር፣ በጸናጽል፣ በበገናና በመሰንቆ ድምፅ የምረቃውን በዓል በደስታ እንዲያከብሩ ከሚኖሩበት ተፈልገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

28. መዘምራኑንም እንደዚሁ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለው ከነጦፋውያን መንደሮች በአንድነት ሰበሰቧቸው።

29. በኢየሩሳሌም ዙሪያ የራሳቸውን መንደሮች ሠርተው ስለ ነበር፣ መዘምራኑን ያመጧቸው ከቤት ጌልገላ፣ ከጌባና ከዓዝምት አካባቢ ነው።

30. ካህናቱና ሌዋውያኑ በሥርዐቱ መሠረት ራሳቸውን ካነጹ በኋላ፣ ሕዝቡን፣ ቅጥሩና በሮቹን አነጹ።

31. እኔም የይሁዳን መሪዎች በቅጥሩ ግንብ አናት ላይ እንዲወጡ አደረግሁ፤ ደግሞም ምስጋና እንዲያቀርቡ ሁለት ታላላቅ የመዘምራን ቡድን መደብሁ። አንዱ በቅጥሩ ግንብ አናት በስተ ቀኝ በኩል “ቈሻሻ መጣያ በር” ወደሚባለው ሄደ።

32. እነዚህንም ሆሻያና ከይሁዳ አለቆች እኩሌቶቹ ተከተሏቸው፤

33. የተከተሏቸውም ከዓዛርያስ፣ ከዕዝራ፣ ከሜሱላም፣

34. ከይሁዳ፣ ከብንያም፣ ከሸማያ፣ ከኤርምያስና፣

35. እንዲሁም መለከት ከያዙ ጥቂት ካህናትና ከአሳፍ ልጅ፣ ከዘኩር ልጅ፣ ከሚካያ ልጅ ከመታንያ ልጅ፣ ከሸማያ ልጅ፣ ከዮናታን ልጅ፣ ከዘካርያስ ጋር ነበር።

36. ወንድሞቹ ሸማያ፣ ኤዝርኤል፣ ሚላላይ፣ ጊላላይ፣ መዓይ፣ ናትናኤል፣ ይሁዳና አናኒም የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ባዘዘው መሠረት የዜማ መሣሪያዎቹን ይዘው ሄዱ፤ ሰልፉን የሚመራውም ጸሓፊው ዕዝራ ነበረ።

37. “ከምንጭ በር” ተነሥተው በቀጥታ ወደ “ዳዊት ከተማ” ደረጃዎች ወጡ፤ ከዚያም በቅጥሩ መውጫ በኩል አድርገው ከዳዊት ቤት በላይ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ወደ “ውሃ በር” ሄዱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 12