ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሩት 2:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እርሷም፣ ‘አጫጆቹን እየተከተልሁ በነዶው መካከል እንድቃርም እባክህ ፍቀድልኝ’ አለችኝ። ለጥቂት ጊዜ በመጠለያው ከማረፏ በስተቀር፣ ወደ አዝመራው ቦታ ገብታ ከጥዋት አንሥቶ እስካሁን ያለ ማቋረጥ ስትቃርም ቈይታለች።”

8. ስለዚህም ቦዔዝ ሩትን፣ “ልጄ ሆይ ስሚኝ፤ ከእንግዲህ ወደ ሌላ አዝመራ ሄደሽ አትቃርሚ፤ ከዚህም አትራቂ፤ ከሴቶች ልጆቼ ጋር እዚሁ ሁኚ።

9. ወንዶቹ የሚያጭዱበትን ዕርሻ ልብ እያልሽ ልጃገረዶቹን ተከተዪ፤ ወንዶቹ እንዳያስቸግሩሽም አስጠንቅቄአቸዋለሁ፤ ውሃ ሲጠማሽ ደግሞ፣ እየሄድሽ ወንዶቹ ሞልተው ካስቀመጡት እንስራ ቀድተሽ ጠጪ።”

10. በዚህ ጊዜ ወደ መሬት ዝቅ ብላ እጅ ነሣችው። እርሷም፣ “ባይተዋር የሆንሁትን እኔን ታስበኝ ዘንድ በፊትህ ሞገስ ለማግኘት የበቃሁት እንዴት ነው?” አለችው።

11. ቦዔዝም መልሶ እንዲህ አላት፤ “ባልሽ ከሞተ ጀምሮ ለዐማትሽ ያደረግሽላትን ሁሉ፣ አባት እናትሽን እንዲሁም የተወለድሽበትን አገር ትተሽ ቀድሞ ከማታውቂው ሕዝብ ጋር ለመኖር እንዴት እንደመጣሽ ነግረውኛል።

12. ስላደረግሽው ሁሉ እግዚአብሔር ዋጋሽን ይክፈልሽ፤ በክንፉ ጥላ ሥር ለመጠለል የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ብድራትሽን አትረፍርፎ ይመልስልሽ።

13. እርሷም መልሳ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ምንም እንኳ፣ ከሴት ሠራተኞችህ እንደ አንዲቱ መቈጠር የማይገባኝ ብሆንም፣ እንድጽናና አድርገኸኛል፤ እንዲሁም እኔን አገልጋይህን በመልካም ንግግር ደስ አሰኝተኸኛል፤ ስለዚህ ሞገስህ እንዳይለየኝ እለምንሃለሁ” አለችው።

14. በምሳ ሰዓት ቦዔዝ፣ “ወደዚህ ቀረብ በዪ፤ እንጀራም ወስደሽ በወይን ሆምጣጤው አጥቅሽ” አላት።እርሷም ከአጫጆች አጠገብ እንደ ተቀመጠች፣ ቦዔዝ የተጠበሰ እሸት ሰጣት፤ የቻለችውንም ያህል በልታ ጥቂት ተረፋት።

15. ለመቃረም ስትነሣም፣ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “በነዶው መካከል እንኳ ብትቃርም ክፉ አትናገሯት፤

16. ይልቁንም ከየታሰረው ነዶ ላይ ጥቂት ጥቂቱን ዘለላ እየመዘዛችሁ በመጣል እንድታነሣው ተዉላት፤ አታስቀይሟት።”

17. ስለዚህ ሩት እስኪመሽ ድረስ ከአዝመራው ላይ ቃረመች፤ ከዚያም የሰበሰበችውን ገብስ ወቃች፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያም ያህል ሆነ።

18. ያንንም ይዛ ወደ ከተማ ሄደች፤ አማቷም የሰበሰበችው ምን ያህል እንደሆነም አየች፤ እንዲሁም ሩት የሚበቃትን ያህል ከበላች በኋላ አስተርፋ የነበረውን አውጥታ ለእርሷ ሰጠቻት።

19. አማቷም፣ “ዛሬ የቃረምሽው ከየት ነው? የትስ ቦታ ስትሠሪ ዋልሽ? መልካም ነገር ያደረገልሽ ሰው የተባረከ ይሁን” አለቻት። ከዚያም ሩት ስትሠራ ስለዋለችበት ስፍራ ባለቤት ለአማቷ ነገረቻት፤ እርሷም፣ “ዛሬ ስቃርም የዋልሁበት አዝመራ ባለቤት፣ ስሙ ቦዔዝ ይባላል” አለቻት።

20. ኑኃሚንም ምራቷን፣ “በጎነቱን ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ማድረጉን ያልተወ እግዚአብሔር ይባርከው” አለቻት፤ ቀጥላም፣ “ሰውየው እኮ የሥጋ ዘመዳችን ነው፤ የመቤዠት ግዴታ ካለባቸው ዘመዶቻችን አንዱ እርሱ ነው” አለቻት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሩት 2