ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሩት 1:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. መሳፍንት በሚገዙበት ዘመን፣ በምድሪቱ ላይ ራብ ሆነ፤ አንድ ሰው በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተ ልሔም ሚስቱንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ፣ ለተወሰነ ጊዜ ለመኖር ወደ ሞዓብ አገር ሄደ።

2. የሰውየው ስም አቤሜሌክ፣ የሚስቱ ኑኃሚን፣ የሁለቱም ወንዶች ልጆቹ ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበሩ። እነርሱም የይሁዳ ቤተ ልሔም ኤፍራታውያን ሲሆኑ፣ ወደ ሞዓብ አገር ሄደው በዚያ ኖሩ።

3. የኑኃሚን ባል አቤሜሌክ ሞተ፤ ኑኃሚንም፣ ከሁለት ልጆቿ ጋር ብቻዋን ቀረች።

4. ልጆቿም ዖርፋና ሩት የተባሉ የሞዓብ ሴቶችን አገቡ፤ በዚያም ዐሥር ዓመት ያህል ከኖሩ በኋላ፣

5. መሐሎንና ኬሌዎን ሁለቱም ሞቱ፤ ኑኃሚንም ሁለት ልጆቿንና ባሏን አጥታ ብቻዋን ቀረች።

6. እርሷም በሞዓብ ሳለች እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘና እህል እንደ ሰጣቸው በሰማች ጊዜ፣ ሁለቱን ምራቶቿን ይዛ ወደ አገሯ ለመመለስ ከዚያ ተነሣች።

7. የኖረችበትን ስፍራ ትታ ከሁለቱ ምራቶቿ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር የሚመልሳቸውን መንገድ ይዘው ጒዞአቸውን ቀጠሉ።

8. ከዚያም ኑኃሚን ሁለቱን ምራቶቿን እንዲህ አለቻቸው፤ “እያንዳንዳችሁ ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ፤ ለሞቱ ባሎቻችሁና ለእኔ በጎ ነገር እንዳደረጋችሁ፣ ለእናንተም እግዚአብሔር እንደዚሁ ያድርግላችሁ፤

9. እያንዳንዳችሁ በምታገቡት ባል ቤት፣ እግዚአብሔር ያሳርፋችሁ።” ከዚያም ሳመቻቸው፤ እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤

10. ቀጥለውም፣ “አይሆንም! ከአንቺ ጋር ተመልሰን ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” አሏት።

11. ኑኃሚን ግን እንዲህ አለቻቸው፤ “ልጆቼ ሆይ፤ ወደየቤታችሁ ተመለሱ፤ ከእኔ ጋር ለምን ትሄዳላችሁ? ባል የሚሆኗችሁ ሌሎች ልጆች ከእንግዲህ የምወልድ ይመስላችኋልን?

12. ወደየቤታችሁ ተመለሱ ልጆቼ፤ ሌላ ባል እንዳላገባ እጅግ አርጅቻለሁ፤ አሁንም ተስፋ አለኝ ብል፣ ዛሬ ማታ አግብቼ ከዚያም ልጆች ብወልድ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሩት 1