ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሩት 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኑኃሚንና ሩት

1. መሳፍንት በሚገዙበት ዘመን፣ በምድሪቱ ላይ ራብ ሆነ፤ አንድ ሰው በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተ ልሔም ሚስቱንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ፣ ለተወሰነ ጊዜ ለመኖር ወደ ሞዓብ አገር ሄደ።

2. የሰውየው ስም አቤሜሌክ፣ የሚስቱ ኑኃሚን፣ የሁለቱም ወንዶች ልጆቹ ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበሩ። እነርሱም የይሁዳ ቤተ ልሔም ኤፍራታውያን ሲሆኑ፣ ወደ ሞዓብ አገር ሄደው በዚያ ኖሩ።

3. የኑኃሚን ባል አቤሜሌክ ሞተ፤ ኑኃሚንም፣ ከሁለት ልጆቿ ጋር ብቻዋን ቀረች።

4. ልጆቿም ዖርፋና ሩት የተባሉ የሞዓብ ሴቶችን አገቡ፤ በዚያም ዐሥር ዓመት ያህል ከኖሩ በኋላ፣

5. መሐሎንና ኬሌዎን ሁለቱም ሞቱ፤ ኑኃሚንም ሁለት ልጆቿንና ባሏን አጥታ ብቻዋን ቀረች።

6. እርሷም በሞዓብ ሳለች እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘና እህል እንደ ሰጣቸው በሰማች ጊዜ፣ ሁለቱን ምራቶቿን ይዛ ወደ አገሯ ለመመለስ ከዚያ ተነሣች።

7. የኖረችበትን ስፍራ ትታ ከሁለቱ ምራቶቿ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር የሚመልሳቸውን መንገድ ይዘው ጒዞአቸውን ቀጠሉ።

8. ከዚያም ኑኃሚን ሁለቱን ምራቶቿን እንዲህ አለቻቸው፤ “እያንዳንዳችሁ ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ፤ ለሞቱ ባሎቻችሁና ለእኔ በጎ ነገር እንዳደረጋችሁ፣ ለእናንተም እግዚአብሔር እንደዚሁ ያድርግላችሁ፤

9. እያንዳንዳችሁ በምታገቡት ባል ቤት፣ እግዚአብሔር ያሳርፋችሁ።” ከዚያም ሳመቻቸው፤ እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤

10. ቀጥለውም፣ “አይሆንም! ከአንቺ ጋር ተመልሰን ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” አሏት።

11. ኑኃሚን ግን እንዲህ አለቻቸው፤ “ልጆቼ ሆይ፤ ወደየቤታችሁ ተመለሱ፤ ከእኔ ጋር ለምን ትሄዳላችሁ? ባል የሚሆኗችሁ ሌሎች ልጆች ከእንግዲህ የምወልድ ይመስላችኋልን?

12. ወደየቤታችሁ ተመለሱ ልጆቼ፤ ሌላ ባል እንዳላገባ እጅግ አርጅቻለሁ፤ አሁንም ተስፋ አለኝ ብል፣ ዛሬ ማታ አግብቼ ከዚያም ልጆች ብወልድ፣

13. እስኪያድጉ ድረስ ትጠብቃላችሁን? እነርሱን በመጠበቅ እስከዚያ ሳታገቡ ትቈያላችሁን? ልጆቼ ሆይ፤ እንዲህ አይሆንም፤ ሁኔታው ከእናንተ ይልቅ ለእኔ እጅግ መራራ ነው፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ተነሥቶአልና።”

14. እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ከዚያም ዖርፋ አማቷን ስማ ተሰናበተቻት፤ ሩት ግን ልትለያት ስላልፈለገች ተጠመጠመችባት።

15. ኑኃሚን መልሳ፣ “እነሆ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች፤ አብረሻት ተመለሽ” አለቻት።

16. ሩት ግን እንዲህ አለች፤ “ተለይቼሽ እንድቀር ወይም እንድመለስ አትለማመጭኝ፤ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትኖሪበትም እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል።

17. በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ እዚያው እቀበራለሁ። ከእንግዲህ ሞት ከሚለየን በቀር ብለይሽ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህም የከፋ ያድርግብኝ።”

18. ሩት አብራት ለመሄድ መቊረጧን በተረዳች ጊዜ፣ ኑኃሚን መጐትጐቷን ተወች።

19. ከዚያም ሁለቱ ሴቶች እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ተጓዙ፤ ቤተ ልሔም እንደ ደረሱም፣ በእነርሱ ምክንያት ከተማው በሙሉ ተተረማመሰ፤ ሴቶቹም፣ “ይህች ኑኃሚን ናትን?” በማለት ተገረሙ።

20. እርሷም እንዲህ አለች፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን እጅግ መራራ አድርጎታልና ማራ በሉኝ እንጂ፣ ኑኃሚን ብላችሁ አትጥሩኝ።

21. በሙላት ወጣሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አስጨንቆኝ፣ ሁሉን የሚችል አምላክ መከራ አምጥቶብኝ ሳለ እንዴት ኑኃሚን ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ?” አለቻቸው።

22. ስለዚህ ኑኃሚን ከምራቷ ከሞዓባዊቷ ሩት ጋር በመሆን ከሞዓብ ተመለሰች፤ ቤተ ልሔም የደረሱትም የገብስ አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅት መጀመሪያ ላይ ነበር።