ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 7:14-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. “በቤቴ የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ነበረብኝ፤ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ፤

15. ስለዚህ አንተን ለማግኘት ወጣሁ፤ፈልጌህ ነበር፤ ይኸው አገኘሁህ።

16. ዐልጋዬን ከግብፅ የመጣ፣ጌጠኛ በፍታ አልብሼዋለሁ።

17. ዐልጋዬን፣የከርቤ፣ የዓልሙንና የቀረፋ ሽቱ አርከፍክፌበታለሁ።

18. ና፤ እስኪነጋ በጥልቅ ፍቅር እንርካ፤በፍቅር ራሳችንን እናስደስት።

19. ባሌ እቤት የለም፤ሩቅ አገር ሄዷል።

20. በገንዘብ የተሞላ ቦርሳ ወስዷል፤ጨረቃዋ ሙሉ እስክትሆን አይመለስም።”

21. በሚያግባቡ ቃላት አሳተችው፤በለሰለሰ አንደበቷ አታለለችው።

22. ለዕርድ እንደሚነዳ በሬ፣ወደ ወጥመድ እንደሚገባ አጋዘን፣ሳያንገራግር ተከተላት፤

23. ፍላጻ ጒበቱን እስኪወጋው ድረስ፣ሕይወቱን እንደሚያሳጣው ሳያውቅ፣በራ ወደ ወጥመድ እንደምትገባ ወፍ ሆነ።

24. ልጆቼ ሆይ፤ አሁንም አድምጡኝ፤የምለውንም ልብ ብላችሁ ስሙኝ።

25. ልባችሁን ወደ መንገዷ አታዘንብሉ፤ወደ ስሕተት ጐዳናዋም አትግቡ።

26. አዋርዳ የጣለቻቸው ብዙ ናቸው፤የገደለቻቸውም ስፍር ቊጥር የላቸውም።

27. ቤቷ ወደ ሲኦል የሚወስድ፣ወደ ሞት ማደሪያም የሚያወርድ ጐዳና ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 7