ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 4:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ልጆቼ ሆይ፤ የአባትን ምክር አድምጡ፤ልብ ብላችሁ ስሙ፤ ማስተዋልንም ገንዘብ አድርጉ።

2. በጎ ትምህርት እሰጣችኋለሁ፤ስለዚህ ትምህርቴን አትተዉ።

3. በአባቴ ቤት ገና ለግላጋ ወጣት፣ለእናቴም አንድ ልጇ ብቻ በነበርሁ ጊዜ፣

4. አባቴ እንዲህ ሲል አስተማረኝ፤“ቃሌን በሙሉ በልብህ ያዝ፤ትእዛዜንም ጠብቅ፤ በሕይወት ትኖራለህ።

5. ጥበብን አግኛት፤ ማስተዋልን ያዛት፤ቃሌን አትርሳ፤ ከእርሷም ዘወር አትበል።

6. ጥበብን አትተዋት፤ እርሷም ከለላ ትሆንሃለች፤አፍቅራት፤ እርሷም ትጠብቅሃለች።

7. ጥበብ ታላቅ ነገር ናት፤ ስለዚህ ጥበብን አግኛት፤ያለህን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት።

8. ክብርን ስጣት፤ ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ዕቀፋት፤ ታከብርሃለች፤

9. በራስህ ላይ ሞገሳማ አክሊል ትደፋልሃለች፤የክብር ዘውድም ታበረክትልሃለች።

10. ልጄ ሆይ፤ አድምጠኝ፤ ቃሌንም ልብ በል፤የሕይወት ዘመንህም ትበዛለች።

11. በጥበብ ጐዳና አስተምርሃለሁ፤ቀጥተኛውንም መንገድ አሳይሃለሁ።

12. ስትሄድ ርምጃህ አይሰናከልም፤ስትሮጥም አትደናቀፍም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 4