ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 13:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ጠቢብ ልጅ የአባቱን ምክር በማስተዋል ይሰማል፤ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አያዳምጥም።

2. ሰው ከከንፈሩ ፍሬ መልካም ነገር ያገኛል፤ወስላቶች ግን ዐመፅን ይናፍቃሉ።

3. አንደበቱን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል፤አፉ እንዳመጣለት የሚናገር ግን ይጠፋል።

4. ሰነፍ አጥብቆ ይመኛል፤ አንዳችም አያገኝም፤የትጉዎች ምኞት ግን ይረካል።

5. ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤ክፉ ሰው ግን ኀፍረትንና ውርደትን ያመጣል።

6. ጽድቅ ቅን የሆነውን ሰው ትጠብቀዋለች፤ክፋት ግን ኀጢአተኛውን ትጥለዋለች።

7. ምንም ሳይኖረው ባለጠጋ መስሎ የሚታይ ሰው አለ፤ሌላው ድኻ መስሎ ይታያል፤ ግን ብዙ ሀብት አለው።

8. የሰው ሀብቱ ለሕይወቱ ቤዛ ሊሆነው ይችላል፤ድኻው ግን ሥጋት የለበትም።

9. የጻድቃን ብርሃን ደምቆ ይበራል፤የክፉዎች መብራት ግን ይጠፋል።

10. ትዕቢት ጠብን ብቻ ያስፋፋል፤ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ትገኛለች።

11. ያላግባብ የተገኘ ገንዘብ እየተመናመነ ያልቃል፤ገንዘቡን ጥቂት በጥቂት የሚያከማች ግን ይጠራቀምለታል።

12. ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል፤የተሳካ ምኞት ግን የሕይወት ዛፍ ነው።

13. ምክርን የሚያቃልል በራሱ ላይ ጥፋት ያመጣል፤ትእዛዝን የሚያከብር ግን ወሮታን ይቀበላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 13