ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 10:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ያላግባብ የተገኘ ሀብት አይጠቅምም፤ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል።

3. እግዚአብሔር ጻድቁ እንዲራብ አያደርግም፤የክፉዎችን ምኞት ግን ያጨናግፋል።

4. ሰነፍ እጆች ሰውን ያደኸያሉ፤ትጉ እጆች ግን ብልጽግናን ያመጣሉ።

5. ሰብሉን በበጋ የሚሰበስብ ጠቢብ ልጅ ነው፤በመከር ጊዜ የሚተኛ ግን ውርደት ይከተለዋል።

6. በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው፤መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል።

7. የጻድቃን መታሰቢያቸው በረከት ነው፤የክፉዎች ስም ግን እንደ ጠፋ ይቀራል።

8. በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝ ይቀበላል፤ለፍላፊ ተላላ ግን ወደ ጥፋት ያመራል።

9. ሐቀኛ ሰው ያለ ሥጋት ይራመዳል፤በጠማማ ጐዳና የሚሄድ ግን ይጋለጣል።

10. በተንኰለኛ ዐይን የሚጠቅስ ሐዘን ያስከትላል፤ለፍላፊ ተላላም ወደ ጥፋት ያመራል።

11. የጻድቅ አንደበት የሕይወት ምንጭ ናት፤መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል።

12. ጥላቻ ጠብን ያነሣሣል፤ፍቅር ግን ስሕተትን ሁሉ ይሸፍናል።

13. ጥበብ በአስተዋይ ሰው ከንፈር ትገኛለች፤በትር ግን ማመዛዘን ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው።

14. ጠቢባን ዕውቀት ያከማቻሉ፤የተላላ አንደበት ግን ጥፋትን ይጋብዛል።

15. የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ድኽነት ግን የድኾች መጥፊያ ናት።

16. የጻድቃን ደመወዝ ሕይወት ታስገኝላቸዋለች፤የክፉዎች ትርፍ ግን ቅጣትን ታመጣባቸዋለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 10