ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሰሎሞን ምሳሌዎች

1. የሰሎሞን ምሳሌዎች፤ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ተላላ ልጅ ግን ለእናቱ ሐዘንን ያተርፋል።

2. ያላግባብ የተገኘ ሀብት አይጠቅምም፤ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል።

3. እግዚአብሔር ጻድቁ እንዲራብ አያደርግም፤የክፉዎችን ምኞት ግን ያጨናግፋል።

4. ሰነፍ እጆች ሰውን ያደኸያሉ፤ትጉ እጆች ግን ብልጽግናን ያመጣሉ።

5. ሰብሉን በበጋ የሚሰበስብ ጠቢብ ልጅ ነው፤በመከር ጊዜ የሚተኛ ግን ውርደት ይከተለዋል።

6. በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው፤መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል።

7. የጻድቃን መታሰቢያቸው በረከት ነው፤የክፉዎች ስም ግን እንደ ጠፋ ይቀራል።

8. በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝ ይቀበላል፤ለፍላፊ ተላላ ግን ወደ ጥፋት ያመራል።

9. ሐቀኛ ሰው ያለ ሥጋት ይራመዳል፤በጠማማ ጐዳና የሚሄድ ግን ይጋለጣል።

10. በተንኰለኛ ዐይን የሚጠቅስ ሐዘን ያስከትላል፤ለፍላፊ ተላላም ወደ ጥፋት ያመራል።

11. የጻድቅ አንደበት የሕይወት ምንጭ ናት፤መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል።

12. ጥላቻ ጠብን ያነሣሣል፤ፍቅር ግን ስሕተትን ሁሉ ይሸፍናል።

13. ጥበብ በአስተዋይ ሰው ከንፈር ትገኛለች፤በትር ግን ማመዛዘን ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው።

14. ጠቢባን ዕውቀት ያከማቻሉ፤የተላላ አንደበት ግን ጥፋትን ይጋብዛል።

15. የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ድኽነት ግን የድኾች መጥፊያ ናት።

16. የጻድቃን ደመወዝ ሕይወት ታስገኝላቸዋለች፤የክፉዎች ትርፍ ግን ቅጣትን ታመጣባቸዋለች።

17. ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ዕርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል።

18. ጥላቻውን የሚሸሽግ ሐሰተኛ አንደበት ያለው ነው፤ሐሜትን የሚዘራ ሁሉ ተላላ ነው።

19. ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።

20. የጻድቅ አንደበት የነጠረ ብር ነው፤የክፉ ሰው ልብ ግን ርባና የለውም።

21. የጻድቃን ከንፈሮች ብዙዎችን ያንጻሉ፤ተላሎች ግን ከማመዛዘን ጒድለት ይሞታሉ።

22. የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤መከራንም አያክልባትም።

23. ተላላ ሰው በክፉ ተግባር ይደሰታል፤አስተዋይ ሰው ግን በጥበብ ደስ ይለዋል።

24. ክፉ ሰው የፈራው ይደርስበታል፤ጻድቅ የሚመኘው ይፈጸምለታል።

25. ዐውሎ ነፋስ ሲነሣ ክፉዎች ተጠራርገው ይወሰዳሉ፤ጻድቃን ግን ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።

26. ሆምጣጤ ጥርስን፣ ጢስ ዐይንን እንደሚጐዳ፣ሰነፍም ለሚልኩት እንዲሁ ነው።

27. እግዚአብሔርን መፍራት ዕድሜን ያረዝማል፤የክፉዎች ዕድሜ ግን በአጭር ይቀጫል።

28. የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤የክፉዎች ተስፋ ግን ከንቱ ሆኖ ይቀራል።

29. የእግዚአብሔር መንገድ ለጻድቃን መጠጊያ፣ክፉ ለሚያደርጉ ግን መጥፊያቸው ነው።

30. ጻድቃን ፈጽሞ አይነቀሉም፤ክፉዎች ግን በምድር አይኖሩም።

31. የጻድቃን አንደበት ጥበብን ያፈልቃል፤ጠማማ ምላስ ግን ትቈረጣለች።