ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 10:16-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. የጻድቃን ደመወዝ ሕይወት ታስገኝላቸዋለች፤የክፉዎች ትርፍ ግን ቅጣትን ታመጣባቸዋለች።

17. ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ዕርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል።

18. ጥላቻውን የሚሸሽግ ሐሰተኛ አንደበት ያለው ነው፤ሐሜትን የሚዘራ ሁሉ ተላላ ነው።

19. ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።

20. የጻድቅ አንደበት የነጠረ ብር ነው፤የክፉ ሰው ልብ ግን ርባና የለውም።

21. የጻድቃን ከንፈሮች ብዙዎችን ያንጻሉ፤ተላሎች ግን ከማመዛዘን ጒድለት ይሞታሉ።

22. የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤መከራንም አያክልባትም።

23. ተላላ ሰው በክፉ ተግባር ይደሰታል፤አስተዋይ ሰው ግን በጥበብ ደስ ይለዋል።

24. ክፉ ሰው የፈራው ይደርስበታል፤ጻድቅ የሚመኘው ይፈጸምለታል።

25. ዐውሎ ነፋስ ሲነሣ ክፉዎች ተጠራርገው ይወሰዳሉ፤ጻድቃን ግን ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።

26. ሆምጣጤ ጥርስን፣ ጢስ ዐይንን እንደሚጐዳ፣ሰነፍም ለሚልኩት እንዲሁ ነው።

27. እግዚአብሔርን መፍራት ዕድሜን ያረዝማል፤የክፉዎች ዕድሜ ግን በአጭር ይቀጫል።

28. የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤የክፉዎች ተስፋ ግን ከንቱ ሆኖ ይቀራል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 10