ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 55:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ፍርሀትና እንቅጥቃጤ መጣብኝ፤ሽብርም ዋጠኝ።

6. እኔም እንዲህ አልሁ፤ “ምነው የርግብ ክንፍ በኖረኝ!በርሬ በሄድሁና ባረፍሁ ነበር፤

7. እነሆ፤ ኰብልዬ በራቅሁ፣በምድረ በዳም በሰነበትሁ ነበር፤ ሴላ

8. ከዐውሎ ነፋስና ከውሽንፍር ሸሽቼ፣ወደ መጠለያዬ ፈጥኜ በደረስሁ ነበር።”

9. ጌታ ሆይ፤ ግፍንና ሁከትን በከተማዪቱ ውስጥ አይቼአለሁና፣ግራ አጋባቸው፤ ቋንቋቸውንም ደበላልቅ።

10. ቀንና ሌሊት ቅጥሯ ላይ ወጥተው ይዞሯታል፤ተንኰልና መከራ በውስጧ አለ።

11. ጥፋት በመካከሏ ይገኛል፤ግፍና አታላይነትም ከጎዳናዋ አይጠፋም።

12. የሚዘልፈኝ ጠላት አይደለምና፤ቢሆንማ ኖሮ በታገሥሁት ነበር፤የሚጠላኝ፣ ራሱንም ቀና ቀና ያደረገብኝ ባላንጣ አይደለም፤ቢሆንማ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር።

13. ነገር ግን አድራጊው አንተ ነህ፤ እኩያዬ፣ ባልንጀራዬና ወዳጄ፤

14. በእግዚአብሔርም ቤት አብረን በሕዝብ መካከል ተመላለስን፤ደስ የሚል ፍቅር በአንድነት ነበረን።

15. ሞት ሳይታሰብ ድንገት ይምጣባቸው፤በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ክፋት በመካከላቸው አድራለችና።

16. እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እጣራለሁ፤ እግዚአብሔርም ያድነኛል።

17. በማታ፣ በጥዋትና በቀትር፣እጮኻለሁ፤ እቃትታለሁም፤እርሱም ድምፄን ይሰማል።

18. በተቃውሞ የተነሡብኝ ብዙዎች ናቸውና፣ከተቃጣብኝ ጦርነት፣ነፍሴን በሰላም ይቤዣታል።

19. አካሄዳቸውን አልቀየሩምና፣እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና፣ከጥንት ጀምሮ በዙፋኑ ላይ ያለ አምላክ፣ ሴላሰምቶ ያዋርዳቸዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 55