ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 22:5-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ወደ አንተ ጮኹ፤ ዳኑም፤በአንተም ታመኑ፤ አላፈሩም።

6. እኔ ግን ትል እንጂ ሰው አይደለሁም፤ሰው ያላገጠብኝ፣ ሕዝብም የናቀኝ ነኝ።

7. የሚያዩኝ ሁሉ ይሣለቁብኛል፤ራሳቸውንም እየነቀነቁ እንዲህ እያሉ ይዘልፉኛል፤

8. “በእግዚአብሔር ተማምኖአል፤እንግዲህ እርሱ ያድነው፤ደስ የተሰኘበትን፣እስቲ ይታደገው።”

9. አንተ ግን ከማሕፀን አወጣኸኝ፤በእናቴም ጡት ሳለሁ፣ መታመኛ ሆንኸኝ።

10. ከማሕፀን ስወጣም በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ከእናቴ ሆድ ጀምሮም አንተ አምላኬ ነህ።

11. መከራ እየተቃረበ ነውና፣የሚረዳኝም የለምና፣ከእኔ አትራቅ።

12. ብዙ ኰርማዎች ከበቡኝ፤ኀይለኛ የባሳን በሬዎችም ዙሪያዬን ቆሙ።

13. እንደሚነጥቅና እንደሚያገሣ አንበሳ፣አፋቸውን ከፈቱብኝ።

14. እንደ ውሃ ፈሰስሁ፤ዐጥንቶቼም ሁሉ ከመጋጠሚያቸው ወለቁ፤ልቤ እንደ ሰም ሆነ፤በውስጤም ቀለጠ።

15. ጒልበቴ እንደ ገል ደረቀ፤ምላሴ ከላንቃዬ ጋር ተጣበቀ፤ወደ ሞት ዐፈርም አወረድኸኝ።

16. ውሾች ከበቡኝ፤የክፉዎች ሸንጎ በዙሪያዬ ተሰልፎአል፤እጆቼንና እግሮቼንም ቸነከሩኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 22