ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 22:17-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ዐጥንቶቼን ሁሉ አንድ በአንድ መቍጠር እችላለሁ፤እነርሱም አፍጥጠው ይመለከቱኛል።

18. ልብሶቼን ተከፋፈሉ፤በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።

19. አንተ ግን፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ፤አጋዤ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

20. ነፍሴን ከሰይፍ ታደጋት፤ውድ ሕይወቴንም ከውሾች ጡጫ አድናት።

21. ከአንበሶች አፍ አድነኝ፤ከአውራሪስ ቀንድም ታደገኝ።

22. ስምህን ለወንድሞቼ እነግራለሁ፤በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ።

23. እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩ፤አወድሱት፤እናንተ የያቆብ ዘር ሁላችሁ፤ አክብሩት፤የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፤ እርሱን ፍሩት።

24. እርሱ የተጨነቀውን ሰው ጭንቀት፣አልናቀም፤ ቸልም አላለምና፤ፊቱንም ከእርሱ አልሰወረም፤ነገር ግን ድረስልኝ ብሎ ሲጮኽ ሰማው።

25. በታላቅ ጉባኤ የማቀርበው ምስጋናዬ ከአንተ የመጣ ነው፤እርሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እፈጽማለሁ።

26. ምስኪኖች በልተው ይጠግባሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹትም ያመሰግኑታል፤ልባችሁም ለዘላለም ሕያው ይሁን!

27. የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስታውሳሉ፤ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ፤የሕዝቦች ነገዶች ሁሉ፣በፊቱ ይሰግዳሉ።

28. መንግሥት የእግዚአብሔር ናትና፤ሕዝቦችንም የሚገዛ እርሱ ነው።

29. የምድር ከበርቴዎች ይበላሉ፤ይሰግዱለታልም፤ነፍሱን በሕይወት ማቆየት የማይችለው፣ ወደ ዐፈር፣ተመላሽ የሆነው ሁሉ በፊቱ ይንበረከካል።

30. የኋለኛው ትውልድ ያገለግለዋል፤ለመጪው ትውልድ ስለ ጌታ ይነገረዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 22