ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 18:38-50 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

38. እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቀቅኋቸው፤ከእግሬም ሥር ወደቁ።

39. አንተ ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፤ባላንጦቼ እግሬ ላይ እንዲደፉ አደረግህ።

40. ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው እንዲሸሹ አደረግህ፤እኔም የሚጠሉኝን አጠፋኋቸው።

41. ለርዳታ ጮኹ፤ የሚያስጥላቸው ግን አላገኙም፤ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም አልመለሰላቸውም።

42. ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ አደቀቅኋቸው፤እንደ መንገድ ላይ ጭቃም አውጥቼ ጣልኋቸው።

43. ከሕዝብ ግርግር አወጣኸኝ፤የሕዝቦች መሪ አድርገህ አስቀመጥኸኝ፤የማላውቀውም ሕዝብ ተገዛልኝ።

44. ትእዛዜን እንደ ሰሙ ይታዘዙልኛል፤ባዕዳንም በፊቴ አንገት ደፉ።

45. ባዕዳን በፍርሃት ተዋጡ፤ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ።

46. እግዚአብሔር ሕያው ነው! ዐምባዬ ይባረክ፤ያዳነኝ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።

47. እርሱ በቀሌን የሚመልስልኝ፣ሕዝቦችንም የሚያስገዛልኝ አምላክ ነው፤

48. ከጠላቶቼም የሚታደገኝ እርሱ ነው።አንተ ከባላንጦቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤ከጨካኞች አዳንኸኝ።

49. እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ስምህንም በመዝሙር እወድሳለሁ።

50. እርሱ ላነገሠው ታላላቅ ድሎችን ይሰጣል፤ጽኑ ፍቅሩንም ለቀባው፣ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይገልጣል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 18