ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 18:18-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. እነርሱ በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ።

19. ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ።

20. እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መልሶልኛል፤እንደ እጄ ንጽሕናም ከፍሎኛል፤

21. የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም።

22. ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ሥርዐቱን ከፊቴ አላራቅሁም።

23. በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ።

24. እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መጠን፣በፊቱም እንደ እጄም ንጽሕና ከፍሎኛል።

25. ከታማኙ ጋር ታማኝ ትሆናለህ፤እንከን ከሌለበት ጋር ያለ እንከን ትሆናለህ፤

26. ከንጹሑ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ለጠማማው አንተ ትጠምበታለህ።

27. አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤ትዕቢተኛውን ዐይን ግን ታዋርዳለህ።

28. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴን ታበራለህ፤አምላኬ ሆይ፤ ጨለማዬን ብርሃን ታደርገዋለህ።

29. በአንተ ጒልበት በሰራዊት ላይ እረማመዳለሁ፤በአምላኬም ኀይል ቅጥር እዘላለሁ።

30. የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው።መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ፣እርሱ ጋሻ ነው።

31. ከእግዚአብሔር በቀር ማን አምላክ አለ?ከአምላካችንስ በቀር ዐምባ ማን ነው?

32. ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣መንገዴንም የሚያቃና እግዚአብሔር ነው።

33. እርሱ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያደርጋል፤በከፍታዎችም ላይ ያቆመኛል።

34. እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናቸዋል፤ክንዴም የናስ ቀስት መገተር ይችላል።

35. የድል ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች፤ዝቅ ብለህም ከፍ አደረግኸኝ።

36. ከሥሬ ያለውን ስፍራ ለአረማመዴ አሰፋህልኝ፤እግሬም አልተንሸራተተም።

37. ጠላቶቼን አሳድጄ ያዝኋቸው፤እስኪጠፉም ወደ ኋላዬ አልተመለስሁም።

38. እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቀቅኋቸው፤ከእግሬም ሥር ወደቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 18