ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መክብብ 8:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ነገሮችን መግለጽ የሚችል፣እንደ ጠቢብ ያለ ሰው ማን ነው?ጥበብ የሰውን ፊት ታበራለች፤የከበደ ገጽታውንም ትለውጣለች።

2. በእግዚአብሔር ፊት መሐላ ስለፈጸምህ፣ የንጉሥን ትእዛዝ አክብር እልሃለሁ።

3. ከንጉሥ ፊት ተጣድፈህ አትውጣ፤ የወደደውንም ማድረግ ስለሚችል ለጥፋት አትሰለፍ።

4. የንጉሥ ቃል የበላይ ስለ ሆነ እርሱን፣ “ምን ታደርጋለህ?” ማን ሊለው ይችላል?

5. እርሱን የሚታዘዝ ሁሉ አይጐዳም፤ጥበበኛም ልብ ትክክለኛውን ጊዜና ተገቢውን አሠራር ያውቃል።

6. የሰው መከራ እጅግ ቢጫነውም፣ለሁሉም ነገር ትክክለኛ ጊዜና ተገቢ አሠራር አለው።

7. ሰው የወደ ፊቱን ስለማያውቅ፣ሊመጣ ያለውን ማን ሊነግረው ይችላል?

8. ሰው ነፋስን መቈጣጠር አይችልም፤በዕለተ ሞቱም ላይ ሥልጣን ያለው ማንም የለም፤በጦርነት ጊዜ ማንም ከግዴታ ነጻ እንደማይሆን፣ክፋትም የሚለማመዷትን አትለቃቸውም።

9. ከፀሓይ በታች የተሠራውን ሁሉ በአእምሮዬ መርምሬ፣ ይህን ሁሉ አየሁ። ሰው ሰውን ለመጒዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።

10. እንዲሁም ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይመጡና ይሄዱ የነበሩት ክፉዎች ተቀብረው አየሁ፤ ይህን ባደረጉበት ከተማም ይመሰገኑ ነበር፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መክብብ 8