ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 9:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የይሩባኣል ልጅ አቤሜሌክ ወደ እናቱ ወንድሞች ወደ ሴኬም ሄደ። እነርሱንና የእናቱን ጐሣዎች በሙሉ እንዲህ አላቸው፤

2. “የሴኬምን ነዋሪዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፤ ‘ሰባዎቹ የይሩባኣል ልጆች ቢገዟችሁ ይሻላል ወይስ አንድ ሰው ብቻ?’ የሥጋችሁ ቍራጭ፣ ያጥንታችሁ ፍላጭ መሆኔን ልብ በሉ።”

3. የእናቱ ዘመዶች ስለ እርሱ ሆነው እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለሴኬም ነዋሪዎች በሙሉ ነገሩ፤ አቤሜሌክንም ለመከተል ልባቸው ዳዳ፤ “እርሱማ ወንድማችን አይደል ብለዋልና”።

4. እነርሱም በኣልብሪት ቤተ ጣዖት ሰባ ሰቅል ናስ ሰጡት፤ አቤሜሌክም በዚያ ወሮበሎችንና ምናምንቴዎችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከተሉት።

5. ከዚያም ዖፍራ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄደ፤ ሰባውን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የይሩበኣል የመጨራሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለ ነበር አመለጠ።

6. የሴኬምና የቤት ሚሎ ነዋሪዎች በሙሉ አቤሜሌክን ለማንገሥ ሴኬም ውስጥ በዐምዱ አጠገብ ካለው የባሉጥ ዛፍ ሥር ተሰበሰቡ።

7. ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ የሴኬም ነዋሪዎች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ፤

8. ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፣ ‘አንተ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

9. የወይራ ዛፍም፣ “ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እግዚአብሔርና ሰዎች የሚከበሩበትን ዘይቴን መስጠት ልተውን?” አለ።

10. “ቀጥሎም ዛፎቹ በለስን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

11. “በለስ ግን፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እጅግ ጣፋጭና መልካም የሆነውን ፍሬዬን መስጠት ልተውን?’ አለ።

12. “ከዚያም ዛፎቹ የወይን ተክልን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

13. “የወይን ተክሉም፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ አማልክትንና ሰዎችን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን መስጠት ልተውን? አለ።

14. በመጨረሻም ዛፎቹ በሙሉ የእሾኽ ቊጥቋጦን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

15. “የእሾኽ ቊጥቋጦውም ዛፎቹን፣ ‘በእርግጥ ቀብታችሁ በላያችሁ የምታነግሡኝ ከሆነ መጥታችሁ በጥላዬ ሥር ተጠለሉ፤ ይህን ባታደርጉ ግን እሳት ከእሾኽ ቊጥቋጦው ይነሣ! የሊባኖስንም ዝግባዎች ይብላ’ አላቸው።

16. “እንግዲህ አቤሜሌክን ስታነግሡት በቅንነትና በእውነት አድርጋችሁት ከሆነ፣ ይሩበኣልንና ቤተ ሰቡን በበጎ ዐይን ተመልክታችሁ ላደረገው የሚገባውን አይታችሁለት ከሆነ፣

17. አባቴ ለእናንተ መዋጋቱን፣ ከምድያማውያን እጅ ሊያድናችሁ ሕይወቱን መስጠቱን አሰባችሁ ማለት ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 9