ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 7:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎችም የምሥራቅ ሕዝቦች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ስፍር ቍጥር አልነበረውም።

13. አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው በሚነግርበት ጊዜ ጌዴዎን እዚያ ደረሰ። ያም ሰው፣ “በሕልሜ ክብ የሆነ አንድ የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባሎ በምድያማውያን ሰፈር ላይ ሲወርድ፣ ድንኳኑንም ሲመታው ከአመታቱም ኀይለኛነት የተነሣ ድንኳኑ ተገልብጦ ሲፈራርስ አየሁ” በማለት ይነግረው ነበር።

14. ጓደኛውም መልሶ፣ “ይህ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታልና” አለው።

15. ጌዴዎንም ሕልሙንና ፍቺውን በሰማ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ወጥቶ፣ “እግዚአብሔር የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ” አላቸው።

16. ሦስቱን መቶ ሰዎች በሦስት ቡድን ከፍሎ፣ እያንዳንዱን ሰው ቀንደ መለከትና በውስጡ ችቦ ያለበት ባዶ ማሰሮ በእጁ እንዲይዝ አደረገ።

17. ጌዴዎንም እንዲህ አላቸው፤ እኔን ተመልከቱ፤ የማደርገውንም አድርጉ፤ በሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ እኔ የማደርገውን አይታችሁ ልክ እንደዚያው አድርጉ።

18. እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን በምንነፋበት ጊዜ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻቸሁን እየነፋችሁ፣ ‘ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን’ ብላችሁ ጩኹ።”

19. ዘቦቹ ተቀያይረው የእኩለ ሌሊቱን ጥበቃ በጀመሩበት ጊዜ፣ ጌዴዎንና አብረውት የነበሩት መቶ ሰዎች በሰፈሩ ዳርቻ ደረሱ፤ እነርሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ የያዟቸውንም ማሰሮች ሰበሩ።

20. በሦስት ቡድን የተከፈሉት ሰዎች ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ ማሰሮቻቸውንም ሰበሩ፤ ችቦዎቻቸውን በግራ እጆቻቸው፣ የሚነፏቸውንም ቀንደ መለከቶች በቀኝ እጆቻቸው ይዘው፣ “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” በማለት ጮኹ።

21. እያንዳንዱ ሰው በሰፈሩ ዙሪያ የተመደበበትን ቦታ እንደያዘም ምድያማውያኑ እየጮኹ ሸሹ።

22. የሦስት መቶው ቀንደ መለከት ድምፅ እንደተሰማም እግዚአብሔር በሰፈሩ ውስጥ ያለው ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤ ሰራዊቱ በጽሬራ አቅጣጫ ወደ ቤት ሺጣ፣ ከዚያም አልፈው በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤላሞሖላ ድንበር ድረስ ሸሽተው ሄዱ።

23. በንፍታሌም፣ በአሴርና በመላው የምናሴ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ተጠርተው ወጡ፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 7