ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 6:7-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ከምድያማውያን ጥቃት የተነሣ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤

8. እግዚአብሔር አንድ ነቢይ ላከላቸው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ።

9. ከግብፃውያን እጅ ታደግኋችሁ፤ ከሚያስ ጨንቋችሁ ሁሉ አዳንኋችሁ፤ እነርሱንም ከፊታችሁ አሳድጄ አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ።

10. እናንተንም፣ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።”

11. የእግዚአብሔር መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፣ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፣ ምድያማውያን እንዳያዩበት ደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር።

12. የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ፣ “አንተ ኀያል ጦረኛ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው።

13. ጌዴዎን መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው።

14. በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ ‘ሂድ፤ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድ ታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው”።

15. ጌዴዎንም፣ “ጌታ ሆይ፤ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ።

16. እግዚአብሔርም፣ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 6