ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 6:23-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. እግዚአብሔርም፣ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው።

24. ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “እግዚአብሔር ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል።

25. በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል።

26. በዚህ ፍርስራሽ ጒብታ ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።”

27. ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተ ሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር።

28. ሌሊቱ ነግቶ የከተማው ሕዝብ ከመኝታው ሲነሣ፣ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ በአጠገቡ የቆመው የአሼራ ምስል ተሰባብሮ፣ አዲስ በተሠራው መሠዊያ ላይ ሁለተኛው ወይፈን ተሠውቶ ነበር።

29. እነርሱም፣ “ይህን ያደረገ ማን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።ነገሩን በጥብቅ ሲከታተሉም፣ “የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን መሆኑን ደረሱበት።”

30. የከተማዪቱም ሰዎች ኢዮአስን፣ “የበኣልን መሠዊያ ያፈረሰና በአጠገቡ የቆመውን የአሼራን ምስል ዐምድ የሰበረው ልጅህ በመሆኑ መሞት ስላለበት አውጣልን አሉት።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 6