ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 4:9-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ዲቦራ መልሳ፣ “ይሁን እሺ፤ መሄዱን አብሬህ እሄዳለሁ፤ በዚህ ሁኔታ የምትሄድ ከሆነ ግን ክብሩ ለአንተ አይሆንም፤ እግዚአብሔር ሲሣራን ለሴት አሳልፎ ይሰጣልና” አለችው። ስለዚህ ዲቦራ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች፤

10. በዚያም ባርቅ ለዛብሎንና ለንፍታሌም ሰዎች ጥሪ አስተላለፈ፤ ዐሥር ሺህ ሰዎች ተከተሉት፤ ዲቦራም አብራው ሄደች።

11. በዚያን ጊዜ ቄናዊው ሔቤር፣ የሙሴ ዐማች የአባብ ልጆች ከሆኑት ከሌሎቹ ቄናውያን ተለይቶ በቃዴስ አጠገብ ጻዕናይም ከተባለ ቦታ ከሚገኘው ትልቅ ወርካ ጥግ ድንኳኑን ተክሎ ነበር።

12. የአቢኒዔም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ መሄዱን ሲሣራ በሰማ ጊዜ፣

13. ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎችንና ከአሪሶት ሐጎይም እስከ ቂሶን ወንዝ ያለውን ሰራዊቱን በሙሉ አሰባሰበ።

14. በዚህ ጊዜ ዲቦራ ባርቅን፣ “ተነሣ! እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሰጠባት ቀን ይህች ናት፤ እነሆ እግዚአብሔር በፊትህ ቀድሞ ወጥቶአል” አለቸው። ስለዚህ ባርቅ ዐሥር ሺህ ሰዎችን አስከትሎ ከታቦር ተራራ ወረደ።

15. እግዚአብሔር ሲሣራንና ሠረገሎቹን ሁሉ በባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት እጅግ ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አደረገ፤ ሲሣራም ከሠረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ፤

16. ባርቅ ግን የሲሣራን ሠረገሎችና ሰራዊቱን እስከ አሪሶት ሐጎይም ድረስ አሳደዳቸው፤ የሲሣራ ሰራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ፤ በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም።

17. በሐጾር ንጉሥ በኢያቡስና በቄናዊው በሔቤር ጐሣ መካከል መልካም ግንኙነት ስለ ነበር ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል ድንኳን ሮጠ።

18. ኢያዔልም ወጥታ ሲሣራን ተቀበለችውና፣ “ጌታዬ፤ ወደ ውስጥ ግባ፤ ፈጽሞ አትፍራ” አለችው፤ ሲሣራም ወደ ድንኳኗ ገባ፤ እርሷም በልብስ ሸፍና ደበቀችው።

19. ሲሣራም፣ “ጠምቶኛልና እባክሽን ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርሷም የወተት ጮጮውን ከፍታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤ እንደ ገናም ሸፈነችው።

20. እርሱም፣ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ፣ “እዚህ ሰው አለ?” ቢልሽ፣ “የለም በይ” አላት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 4