ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 20:32-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. ብንያማውያኑ፣ “እንደ በፊቱ ይኽው ድል እያደረግናቸው ነው” አሉ፣ እስራኤላውያንም በበኩላቸው፣ “ወደ ኋላ እያፈገፈግን ከከተማዪቱ ወደ መንገዶቹ እንዲርቁ እናድርጋቸው” ይሉ ነበር።

33. የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከነበሩበት ቦታ አፈግፍገው በበኣልታማር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። ሸምቆ ይጠባበቅ የነበረው የእስራኤል ጦር ደግሞ ካደፈጠበት ከጊብዓ በስተ ምዕራብ ካለው ቦታ ወጣ።

34. ከዚያም ከመላው እስራኤል የተውጣጣው ዐሥር ሺህ ጦር በጊብዓ ላይ ፊት ለፊት አደጋ ጣለ። ውጊያው ከመበርታቱ የተነሣም፣ ብንያማውያን መጥፊያቸው እየቀረበ መምጣቱን ገና አላወቁም ነበር።

35. እግዚአብሔር ብንያምን በእስራኤል ፊት መታው፤ በዚያችም ዕለት እስራኤላውያን በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ብንያማውያንን ገደሉ።

36. ከዚህ የተነሣ ብንያማውያን ድል መሆናቸውን ተረዱ።በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ስለ ተማመኑ የተሸነፉ በመምሰል ለብንያማውያን ቦታ ለቀቁ።

37. ከዚያም ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በድንገት እየተወረወሩ ወደ ጊብዓ ገቡ፤ በየቦታው ተሰራጭተውም መላዪቱን ከተማ በሰይፍ መቱ።

38. የእስራኤል ሰዎች ያሸመቀው ጦር በከተማዪቱ ውስጥ ከባድ የጢስ ደመና ምልክት እንዲያሳይ፤

39. እስራኤላውያንም ይህን ሲያዩ ወዲያውኑ እንዲያፈገፍጉ ተስማሙ።ብንያማውያንን ማጥቃት እንደ ጀመሩ፣ ሠላሳ እስራኤላውያንን ስለ ገደሉ፣ “እንደ መጀመሪያው የጦርነት ጊዜ እያሸነፍናቸው ነው” አሉ።

40. ነገር ግን የጢሱ ዐምድ ከከተማዪቱ መነሣት በጀመረ ጊዜ፣ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ዞረው የመላዪቱ ከተማ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ።

41. ከዚያም እስራኤላውያን ዞረው አጠቋቸው፤ በዚህ ጊዜ ብንያማውያን ጥፋት እንደ ደረሰባቸው ስላወቁ እጅግ ደነገጡ።

42. ስለዚህም ጀርባቸውን አዙረው ከእስራኤላውያን ፊት ወደ ምድረ በዳው ሸሹ፤ ሆኖም ከጦርነት ማምለጥ አልቻሉም፤ ከየከተሞቹ የወጡ እስራኤላውያንም በዚያው ገደሏቸው።

43. ብንያማውያንንም ከበቧቸው፤ አሳደዷቸው፤ ከጊብዓ በስተ ምሥራቅ ትይዩ ባለውም ስፍራ በቀላሉ አሸነፏቸው፤

44. በጦርነቱም ላይ ዐሥራ ስምንት ሺህ ብንያማውያን ወደቁ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ።

45. ብንያማውያን ጀርባቸውን አዙረው በምድረ በዳው በኩል ወደ ሬሞን ዐለት በሚሸሹበት ጊዜ፣ እስራኤላውያን በመንገድ ላይ አምስት ሺህ ሰው ገደሉባቸው፤ እስከ ጊድአምም ድረስ ተከታትለው ሁለት ሺህ ሰዎች በተጨማሪ ገደሉ።

46. በዚያች ዕለት ሰይፍ የታጠቊ ሃያ አምስት ሺህ ብንያማውያን በጦር ሜዳ ወደቊ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 20