ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 20:20-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. የእስራኤል ሰዎች ብንያማውያንን ለመውጋት ሄዱ፤ በጊብዓ ለሚያደርጉትም ውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

21. ብንያማውያን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚያችም ዕለት ከእስራኤላውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

22. ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ተበረታትተው በመጀመሪያው ቀን ተሰልፈው በነበረበት ስፍራ ላይ እንደ ገና ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

23. እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሱ፤ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመግጠም እንደ ገና እንውጣን?” ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ውጡና ግጠሟቸው” ብሎ መለሰላቸው።

24. በሁለተኛው ቀን እስራኤላውያን ወደ ብንያማውያን ተጠጉ።

25. በዚሁ ጊዜም ብንያማውያን፣ እስራኤላውያንን ሊወጉ ከጊብዓ ወጡ፤ እንደ ገናም በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

26. የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እዚያም እያለቀሱ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያን ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ።

27. እስራኤላውያንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቁ፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት እዚያው ነበር፤

28. የአሮን ልጅ፤ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም በፊቱ ይቆም ነበር። እስራኤላውያንም፣ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን እንደ ገና ሄደን ጦርነት እንግጠማቸው ወይስ ይቅር?” ሲሉ ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “ሂዱ፤ በነገው ዕለት በእጃችሁ እሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው።

29. ከዚያም እስራኤላውያን በጊብዓ ዙሪያ ድብቅ ጦር አኖሩ።

30. በሦስተኛውም ቀን ብንያማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ጊብዓን ለመውጋት ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

31. ብንያማውያንም ሊገጥሟቸው ወጡ፤ ከከተማዪቱም ርቀው እንዲሄዱ ተደረጉ፤ እንደ በፊቱም እስራኤላውያንን ይገድሉ ጀመር። ከዚህ የተነሣም በሜዳው እንዲሁም ወደ ቤቴልና ወደ ጊብዓ በሚወስደው መንገዶች ላይ ሠላሳ ያህል ሰዎች ወድቀው ነበር።

32. ብንያማውያኑ፣ “እንደ በፊቱ ይኽው ድል እያደረግናቸው ነው” አሉ፣ እስራኤላውያንም በበኩላቸው፣ “ወደ ኋላ እያፈገፈግን ከከተማዪቱ ወደ መንገዶቹ እንዲርቁ እናድርጋቸው” ይሉ ነበር።

33. የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከነበሩበት ቦታ አፈግፍገው በበኣልታማር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። ሸምቆ ይጠባበቅ የነበረው የእስራኤል ጦር ደግሞ ካደፈጠበት ከጊብዓ በስተ ምዕራብ ካለው ቦታ ወጣ።

34. ከዚያም ከመላው እስራኤል የተውጣጣው ዐሥር ሺህ ጦር በጊብዓ ላይ ፊት ለፊት አደጋ ጣለ። ውጊያው ከመበርታቱ የተነሣም፣ ብንያማውያን መጥፊያቸው እየቀረበ መምጣቱን ገና አላወቁም ነበር።

35. እግዚአብሔር ብንያምን በእስራኤል ፊት መታው፤ በዚያችም ዕለት እስራኤላውያን በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ብንያማውያንን ገደሉ።

36. ከዚህ የተነሣ ብንያማውያን ድል መሆናቸውን ተረዱ።በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ስለ ተማመኑ የተሸነፉ በመምሰል ለብንያማውያን ቦታ ለቀቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 20