ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 18:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ካህኑም፣ “በሰላም ሂዱ፤ መንገዳችሁን እግዚአብሔር አቃንቶላችኋል” ብሎ መለሰላቸው።

7. ስለዚህ አምስቱ ሰዎች ከዚያ ተነሥተው ወደ ላይሽ መጡ፤ ሲዶናውያን ያለ ስጋት በጸጥታ እንደሚኖሩ ሁሉ፣ በዚያም የሚኖረው ሕዝብ በሰላም እንደሚኖር አዩ። ምድሪቱ አንዳች የሚጐድላት ነገር ባለመኖሩ ሕዝቡ ባለጸጋ ነበር። እንዲሁም ከሲዶናውያን ርቆ የሚኖር ሲሆን፣ ከማንኛውም ሕዝብ ጋር ግንኙነት አልነበረውም።

8. ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል እንደ ተመለሱ ወገኖቻቸው፣ “የሄዳችሁበት ጒዳይ እንዴት ሆነ?” በማለት ጠየቋቸው።

9. መልእክተኞቹም እንዲህ አሏቸው፤ “ምድሪቱ እጅግ መልካም መሆኗን አይተናል፤ እንግዲህ ተነሡ! ሄደን እንዋጋቸው፤ ተነሡ እንጂ ዝም ትላላችሁን? ወደዚያው ሄዳችሁ ምድሪቱን ለመያዝ አታመንቱ

10. እዚያ ስትደርሱም ያለ ሥጋት የሚኖር ሕዝብ፣ እግዚአብሔር በእጃችሁ የሚሰጣችሁን አንዳች ነገር ያልጐደላትን ሰፊ ምድር ታገኛላችሁ።”

11. ከዚያ በኋላም ከዳን ወገን ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ስድስት መቶ ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሡ።

12. ወጥተውም በይሁዳ ምድር ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ እንግዲህ ከቂርያትይዓሪም በስተ ምዕራብ ያለው ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር መባሉ ከዚሁ የተነሣ ነው።

13. ከዚያም ተጒዘው ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር በመሄድ ወደ ሚካ ቤት መጡ።

14. የላይሽን ምድር ሰልለው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ለወንድሞቻቸው፣ “ከእነዚሁ ቤቶች በአንዱ ኤፉድ፣ ተራፊም፣ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት እንዳለ ታውቃላችሁን? እንግዲህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ዕወቁበት” አሏቸው።

15. ስለዚህ ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበት ወደ ሚካ ቤት ጎራ ብለው ሰላምታ አቀረቡለት።

16. ለጦርነት ተዘጋጅተው የመጡት ስድስት መቶ የዳን ሰዎች በቅጥሩ በር መግቢያ ላይ ቆመው ነበር።

17. ካህኑ ለጦርነት ከተዘጋጁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋር በቅጥሩ በር ላይ ቆሞ ሳለ፣ ምድሪቱን ለመሰለል መጥተው የነበሩትን አምስት ሰዎች ወደ ቤቱ ውስጥ በመግባት የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል ወሰዱ።

18. እነዚህ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በሚወስዱበት ጊዜ ካህኑ፣ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” አላቸው።

19. እነርሱም፣ “ዝም በል! አንዲት ቃል እንዳትተነፍስ፤ ከእኛ ጋር ሁን፤ አባትም ካህንም ሁነን፤ ለአንተስ የአንድ ቤተ ሰብ ካህን ከመሆን ይልቅ በእስራኤል የአንዱ ነገድና ጐሣ ካህን ሆነህ ማገልገሉ አይሻልህምን?” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 18