ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 18:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. የላይሽን ምድር ሰልለው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ለወንድሞቻቸው፣ “ከእነዚሁ ቤቶች በአንዱ ኤፉድ፣ ተራፊም፣ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት እንዳለ ታውቃላችሁን? እንግዲህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ዕወቁበት” አሏቸው።

15. ስለዚህ ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበት ወደ ሚካ ቤት ጎራ ብለው ሰላምታ አቀረቡለት።

16. ለጦርነት ተዘጋጅተው የመጡት ስድስት መቶ የዳን ሰዎች በቅጥሩ በር መግቢያ ላይ ቆመው ነበር።

17. ካህኑ ለጦርነት ከተዘጋጁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋር በቅጥሩ በር ላይ ቆሞ ሳለ፣ ምድሪቱን ለመሰለል መጥተው የነበሩትን አምስት ሰዎች ወደ ቤቱ ውስጥ በመግባት የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል ወሰዱ።

18. እነዚህ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በሚወስዱበት ጊዜ ካህኑ፣ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” አላቸው።

19. እነርሱም፣ “ዝም በል! አንዲት ቃል እንዳትተነፍስ፤ ከእኛ ጋር ሁን፤ አባትም ካህንም ሁነን፤ ለአንተስ የአንድ ቤተ ሰብ ካህን ከመሆን ይልቅ በእስራኤል የአንዱ ነገድና ጐሣ ካህን ሆነህ ማገልገሉ አይሻልህምን?” አሉት።

20. ይህም ካህኑን ደስ አሰኘው፤ እርሱም ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና የተቀረጸውን ምስል ይዞ ከሕዝቡ ጋር ሄደ።

21. እነርሱም ሕፃናታቸውን፣ የከብቶቻቸውን መንጋና ሀብታቸውን ሁሉ ወደ ፊት በማስቀደም ተመልሰው ሄዱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 18