ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሳምሶንና ደሊላ

1. አንድ ቀን ሳምሶን ወደ ጋዛ ሄደ፤ እዚያም አንዲት ዝሙት አዳሪ አየ፤ አብሮአት ለማደርም ገባ።

2. የጋዛ ሰዎች፣ “ሳምሶን እዚህ ነው!” የሚል ወሬ ደረሳቸው፤ ስለዚህም ሰዎቹ ቦታውን ከበው፤ ሌሊቱን በሙሉ በከተማዪቱ ቅጥር በር ላይ አድፍጠው ጠበቊት፤ “በማለዳ እንገድለዋለን” በማለትም ሌሊቱን በሙሉ እንዳደፈጡ አደሩ።

3. ነገር ግን ሳምሶን እዚያ የተኛው እስከ እኩለ ሌሊት ብቻ ነበር፤ ተነሥቶም የከተማዪቱን ቅጥር በር ከሁለት መቃኖቹ ጋር መወርወሪያውንና ማያያዣውን ጭምር በሙሉ ነቅሎ በትከሻው ላይ ካደረገ በኋላ፣ በኬብሮን ፊት ለፊት እስካለው ኰረብታ ጫፍ ድረስ ተሸክሞት ወጣ።

4. ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ።

5. የፍልስጥኤማውያን ገዦች ወደ እርሷ ሄደው፣ “እርሱን አስረን በቊጥጥራችን ሥር በማዋል ልናሸንፈው እንዴት እንደምንችልና የብርታቱ ታላቅነት ምስጢር ምን እንደሆነ እንዲያሳይሽ እስቲ አባብዪው፤ ይህን ካደረግሽ እያንዳንዳችን አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰቅል ጥሬ ብር እንሰጥሻለን” አሏት።

6. ስለዚህም ደሊላ ሳምሶንን፣ “የብርታትህን ታላቅነት ምስጢርና ታስረህ በቊጥጥር ሥር የምትውለው እንዴት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለችው።

7. ሳምሶንም፣ “ማንም ባልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች ቢያስረኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።

8. ከዚያም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ያልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች አመጡላት፤ እርሷም አሰረችው።

9. ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፣ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው፤ ሳምሶን ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚ በጣጠስ ጠፍሮቹን በቀላሉ በጣጠሳቸው፤ ስለዚህ የብርታቱ ምስጢር ምን እንደሆነ ሊታወቅ አልቻለም።

10. ደሊላም ሳምሶንን፣ “አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል፤ እባክህ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል ንገረኝ” አለችው።

11. እርሱም፣ ሥራ ላይ ባልዋሉ አዳዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።

12. ደሊላም አዳዲስ ገመዶች ወስዳ አሰረችው፤ ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፣ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። እርሱ ግን ክንዱ የታሰረባቸውን ገመዶች እንደ ፈትል ክር በጣጠሳቸው።

13. ደግሞም ደሊላ ሳምሶንን፣ “እስካሁን አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል። እባክህን አንተን ማሰር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ንገረኝ” አለችው።እርሱም መልሶ፣ “የራስ ጠጒሬን ሰባት ቈንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጒነሽ በችካል ብትቸክዪው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። ደሊላም መተኛቱን አይታ ሰባቱን ቈንዳላዎቹን ከድር ጋር ጐነጐነችው፤

14. ከችካልም ጋር ቸከለችው።እንደ ገናም፣ “ሳምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ችካሉን ከነድሩ፣ ከነቈንዳላው ነቀለው።

15. ከዚያም፣ “ሳታምነኝ እንዴት ‘እወድሻለሁ’ ትለኛለህ? ስታታልለኝና የኀይልህንም ታላቅነት ምስጢር ስትደብቀኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው” አለችው።

16. በሕይወት መኖሩን እስኪጠላ ድረስ ዕለት ዕለት በመጨቅጨቅ አሰለቸችው።

17. ስለዚህ ሁሉንም ነገር ነገራት፤ እንዲህም አለ፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆንሁ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም፤ የራሴ ጠጒር ቢላጭ ግን ኀይሌ ተለይቶኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።

18. ደሊላ ሁሉንም ነገር እንደ ነገራት በተረዳች ጊዜ፣ ለፍልስጥኤማውያን ገዦች “ሁሉንም ነገር ነግሮኛልና ተመልሳችሁ ኑ” ብላ ላከችባቸው፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም ብሩን ይዘው ተመልሰው መጡ።

19. ደሊላ፣ ሳምሶንን በጭኗ ላይ አስተኝታ እንቅልፍ እንዲወስደው ካደረገች በኋላ አንድ ሰው ጠርታ ሰባቱን የጠጒር ቈንዳላዎቹን አስላጨቻቸው፤ እርሷም ታስጨንቀው ጀመር፤ ኀይሉም ተለየው።

20. እርሷም፣ “ሳምሶን፤ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” አለችው።ሳምሶን ከእንቅልፉ ነቅቶ፣ “እንደ ወትሮው አደርጋለሁ” አለ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ተወው አላወቀም ነበር።

21. ከዚያም ፍልስጥኤማውያን ያዙት፤ ዐይኖቹን አውጥተው ወደ ጋዛ ይዘውት ወረዱ፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም እስር ቤት ውስጥ እህል እንዲፈጭ አደረጉት፤

22. ነገር ግን ከተላጨ በኋላ ጠጒሩ እንደ ገና ማደግ ጀመረ።

የሳምሶን አሟሟት

23. በዚህ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን ገዦች፣ “አምላካችን ዳጎን፣ ጠላታችን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል” ብለው በመደሰት ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ ተሰበሰቡ።

24. ሕዝቡም ሳምሶንን ባዩት ጊዜ፣ አምላካቸውን ዳጎንን በማመስገን፣“ምድራችንን ያጠፋውን፣ብዙ ሰው የገደለብንን፣ ጠላታችንን፣አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” አሉ።

25. እጅግ ደስ ባላቸው ጊዜ፣ “እንዲያዝናናን ሳምሶንን አምጡት” አሉ፤ ስለዚህ ሳምሶንን ከእስር ቤት ጠርተው አስመጡት፤ በፊታቸውም ተጫወተ።በምሶሶዎቹ መካከል ባቆሙት ጊዜ፣

26. ሳምሶን እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ፣ “ቤተ ጣዖቱ ደግፈው ወደ ያዙት ምሰሶዎች አስጠጋኝና ልደገፋቸው” አለው።

27. በዚህ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ቤተ ጣዖቱን ሞልተውት ነበር፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም በሙሉ በዚያ ነበሩ፤ ሳምሶን ሲጫወት ለማየት ሦስት ሺህ ያህል ወንዶችና ሴቶች በጣራው ላይ ነበሩ።

28. ሳምሶንም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፤ እባክህን አንድ ጊዜ ብቻ ብርታት ስጠኝና ስለ ጠፉት ዐይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አንዴ ልበቀላቸው።”

29. ከዚያም ቤተ ጣዖቱን መካከል ላይ ደግፈው የያዙትን ሁለት ምሰሶዎች አንዱን በቀኙ፣ አንዱን በግራ እጁ አቅፎ በመያዝ፣

30. “ከፍልስጥኤማውያን ጋር አብሬ ልሙት” በማለት ባለ ኀይሉ ሲገፋው፣ ቤተ ጣዖቱ በገዦቹና በውስጡ በነበሩት በሌሎቹ ሰዎች ሁሉ ላይ ወደቀባቸው፤ ስለዚህ በሕይወት ከኖረበት ጊዜ ይልቅ በሞቱ ጊዜ ብዙ ሰው ገደለ።

31. ወንድሞቹና መላው የአባቱ ቤተ ሰብ ሬሳውን ለማምጣት ወደዚያ ወረዱ፤ አምጥተውም የአባቱ የማኑሄ መቃብር ባለበት በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ቀበሩት። ሳምሶን በእስራኤል ላይ ሃያ ዓመት ፈራጅ ሆነ።