ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 14:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሳምሶን ወደ ተምና ወረደ፤ እዚያም አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አየ።

2. እንደተመለሰም አባቱንና እናቱን፣ “በተምና አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አይቻለሁና አሁኑኑ አጋቡኝ” አላቸው።

3. አባቱና እናቱም፣ “ከዘመዶችህ ወይም ከሕዝባችን ሁሉ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት መች ታጣችና ነው ወዳልተገረዙት ፍልስጥኤማውያን ሚስት ፍለጋ የሄድኸው?” አሉት።ሳምሶንም አባቱን፣ “ልቤን የማረከችው እርሷ ናትና እርሷን አጋባኝ” አለው።

4. በዚያን ጊዜ በእስራኤል ላይ ገዦቹ ፍልስጥኤማውያን ስለ ነበሩ፣ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጠብ እንዲፈጠር እግዚአብሔር ሆን ብሎ ያደረገው ነገር መሆኑን አባቱና እናቱ አላወቁም ነበር።

5. ከዚያም ሳምሶን ከአባቱና ከእናንቱ ጋር ወደ ተምና ወረደ፤ በዚያም ከአንድ የወይን አትክልት ቦታ እንደ ደረሱ፣ ድንገት አንድ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት።

6. በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ስለዚህ የፍየል ጠቦት እንደሚገነጣጠል አንበሳውን ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጠለው፤ ያደረገውን ግን ለአባቱም ሆነ ለእናቱ አልነገራቸውም ነበር።

7. ወደ ሴቲቱም ወረደ፤ ከእርሷም ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ወደዳት።

8. ከጥቂት ቀን በኋላም ሊያገባት ተመለሰ፤ የአንበሳውንም በድን ለማየት ከመንገድ ዘወር አለ፤ በበድኑም ውስጥ የንብ መንጋ ሰፍሮ ተመለከተ፤ ማርም ነበረበት፤

9. በእጁ ወስዶም መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ከወላጆቹም ጋር እንደተገናኘም ከማሩ ሰጣቸው፤ እነርሱም በሉ። ነገር ግን ማሩን የወሰደው ከአንበሳ በድን መሆኑን አልነገራቸውም ነበር።

10. የሳምሶን አባት ልጅቱን ሊያይ ወረደ፤ ሳምሶንም በነበረው የሙሽራ ወግ መሠረት በዚያ ግብዣ አደረገ።

11. እርሱም ለፍልስጥኤማውያን በታየ ጊዜ፣ ሠላሳ አጃቢዎች ሰጡት።

12. ሳምሶን እንዲህ አላቸው፤ አንድ እንቈቅልሽ እነግራችኋለሁ፤ ታዲያ ፍቺውን በሰርጉ በዓል ሰባት ቀኖች ውስጥ ከሰጣችሁኝ፣ ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳ የክት ልብስ እሰጣችኋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 14