ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 13:9-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሴቲቱ በዕርሻ ውስጥ ሳለች ተገለጠላት፤ በዚህ ጊዜ ግን ባሏ ማኑሄ አብሮአት አልነበረም።

10. እርሷም ለባሏ ለመንገር ፈጥና በመሄድ፣ “ባለፈው ጊዜ የተገለጠልኝ ሰው ዛሬም ተገለጠልኝ” አለችው።

11. ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተላት፤ ሰውየው እንደ ደረሰም፣ “ከሚስቴ ጋር ተነጋግረህ የነበርኸው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፤ “አዎን እኔ ነኝ” አለው።

12. ማኑሄም፣ “ያልኸው በሚፈጸምበት ጊዜ የልጁ ሕይወት የሚመራው እንዴት ነው? እኛስ ምን ማድረግ አለብን?” ሲል ጠየቀው።

13. የእግዚአብሔርም መልአክ እንዲህ አለው፤ “ሚስትህ የነገርኋትን ሁሉ ታድርግ።

14. ከወይን ተክል የሚገኝ ማንኛውንም ነገር አትብላ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ ርኵስ ነገር አትብላ፤ ያዘዝኋትንም ሁሉ ታድርግ።”

15. ከዚያም ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ፣ “የፍየል ጠቦት ዐርደን እስክናዘጋጅልህ ድረስ እባክህ ቈይ” አለው።

16. የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “የግድ ብታቈየኝ እንኳ የምታቀርበውን ማንኛውንም ምግብ አልበላም፤ ነገር ግን የሚቃጠል መሥዋዕት የምታዘጋጅ ከሆነ እርሱን ለእግዚአብሔር አቅርበው” አለው። የሚያነጋግረው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር።

17. ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ፣ “የተናገርኸው ሲፈጸም እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?” በማለት ጠየቀው።

18. እርሱም፣ “ስሜ ድንቅ ስለ ሆነ፣ ለምን ትጠይቀኛለህ?” አለው።

19. ማኑሄም የፍየሉን ጠቦት ከእህል ቍርባኑ ጋር ወስዶ በዐለት ላይ ለእግዚአብሔር ሠዋው። ማኑሄና ሚስቱ እያዩ እግዚአብሔር አስደናቂ ነገር አደረገ፤

20. ይኸውም የእሳቱ ነበልባል ከመሠዊያው ወደ ሰማይ ሲወጣ፣ የእግዚአብሔር መልአክ በነበልባሉ ውስጥ ዐረገ። ማኑሄና ሚስቱ ይህን ሲመለከቱ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ።

21. የእግዚአብሔርም መልአክ ለማኑሄና ለሚስቱ ዳግመኛ ባለመገለጡ፣ ቀደም ሲል የተገለጠላቸው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ማኑሄ ዐወቀ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 13