ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 13:9-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሴቲቱ በዕርሻ ውስጥ ሳለች ተገለጠላት፤ በዚህ ጊዜ ግን ባሏ ማኑሄ አብሮአት አልነበረም።

10. እርሷም ለባሏ ለመንገር ፈጥና በመሄድ፣ “ባለፈው ጊዜ የተገለጠልኝ ሰው ዛሬም ተገለጠልኝ” አለችው።

11. ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተላት፤ ሰውየው እንደ ደረሰም፣ “ከሚስቴ ጋር ተነጋግረህ የነበርኸው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፤ “አዎን እኔ ነኝ” አለው።

12. ማኑሄም፣ “ያልኸው በሚፈጸምበት ጊዜ የልጁ ሕይወት የሚመራው እንዴት ነው? እኛስ ምን ማድረግ አለብን?” ሲል ጠየቀው።

13. የእግዚአብሔርም መልአክ እንዲህ አለው፤ “ሚስትህ የነገርኋትን ሁሉ ታድርግ።

14. ከወይን ተክል የሚገኝ ማንኛውንም ነገር አትብላ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ ርኵስ ነገር አትብላ፤ ያዘዝኋትንም ሁሉ ታድርግ።”

15. ከዚያም ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ፣ “የፍየል ጠቦት ዐርደን እስክናዘጋጅልህ ድረስ እባክህ ቈይ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 13