ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 13:3-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ አንቺ መካን ነሽ፤ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ።

4. እንግዲህ ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኵስ ነገርም አትብዪ፤

5. ምክንያቱም ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ልጁ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል።”

6. ከዚያም ሴቲቱ ወደ ባሏ ሄዳ እንዲህ አለችው፤ “የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፤ የእግዚአብሔር መልአክ የሚመስልና እጅግ የሚያስደነግጥ ነበር። ከየት እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፤ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤

7. ነገር ግን፣ ‘ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኵስ ነገር አትብዪ፤ ልጁም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና’ ብሎኛል።”

8. ከዚያም ማኑሄ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ አንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ”። ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

9. እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሴቲቱ በዕርሻ ውስጥ ሳለች ተገለጠላት፤ በዚህ ጊዜ ግን ባሏ ማኑሄ አብሮአት አልነበረም።

10. እርሷም ለባሏ ለመንገር ፈጥና በመሄድ፣ “ባለፈው ጊዜ የተገለጠልኝ ሰው ዛሬም ተገለጠልኝ” አለችው።

11. ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተላት፤ ሰውየው እንደ ደረሰም፣ “ከሚስቴ ጋር ተነጋግረህ የነበርኸው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፤ “አዎን እኔ ነኝ” አለው።

12. ማኑሄም፣ “ያልኸው በሚፈጸምበት ጊዜ የልጁ ሕይወት የሚመራው እንዴት ነው? እኛስ ምን ማድረግ አለብን?” ሲል ጠየቀው።

13. የእግዚአብሔርም መልአክ እንዲህ አለው፤ “ሚስትህ የነገርኋትን ሁሉ ታድርግ።

14. ከወይን ተክል የሚገኝ ማንኛውንም ነገር አትብላ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ ርኵስ ነገር አትብላ፤ ያዘዝኋትንም ሁሉ ታድርግ።”

15. ከዚያም ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ፣ “የፍየል ጠቦት ዐርደን እስክናዘጋጅልህ ድረስ እባክህ ቈይ” አለው።

16. የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “የግድ ብታቈየኝ እንኳ የምታቀርበውን ማንኛውንም ምግብ አልበላም፤ ነገር ግን የሚቃጠል መሥዋዕት የምታዘጋጅ ከሆነ እርሱን ለእግዚአብሔር አቅርበው” አለው። የሚያነጋግረው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር።

17. ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ፣ “የተናገርኸው ሲፈጸም እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?” በማለት ጠየቀው።

18. እርሱም፣ “ስሜ ድንቅ ስለ ሆነ፣ ለምን ትጠይቀኛለህ?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 13