ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 1:9-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሰዎች በኰረብታማው አገር፣ በኔጌብና በምዕራቡ ኮረብታ ግርጌ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ወረዱ፤

10. ቀደም ሲል ቂርያት አርባቅ ተብላ በምትጠራው በኬብሮን በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ድል አደረጉ።

11. ከዚያም ቀደም ሲል ቅርያትሤፍር ተብላ በምትጠራው በዳቤር በሚኖሩት ሰዎች ላይ ዘመቱ።

12. ካሌብም፣ “ቅርያት ሤፍርን ወግቶ ለሚይዛት ሰው ልጄን ዓክሳንን እድርለታለሁ” አለ።

13. በዚህ ጊዜ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዘ፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳንን ዳረለት።

14. እርሷም ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜ፣ አባቷ የዕርሻ መሬት እንዲሰጠው ይለምነው ዘንድ አጥብቃ ነገረችው፤ ካሌብም እርሷ ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

15. እርሷም፣ “እባክህ አንድ ነገር አድርግልኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።

16. የቄናዊው የሙሴ ዐማት ዝርያዎች ከዓራድ አጠገብ በኔጌብ ውስጥ በይሁዳ ምድረ በዳ ካሉት ሕዝቦች ጋር አብረው ለመኖር፣ ከይሁዳ ሰዎች ጋር በመሆን ከባለ ዘንባባዋ ከተማ ከኢያሪኮ ወጡ።

17. የይሁዳ ሰዎች ከወንድሞቻቸው ከስምዖን ልጆች ጋር ሆነው በጻፋት በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ከተማዪቱንም ፈጽሞ ደመሰሷት፤ ስለዚህ ከተማዪቱ ሔርማ ተብላ ተጠራች።

18. ደግሞም የይሁዳ ሰዎች ጋዛ፣ አስቀሎና፣ አቃሮን የተባሉትን ከተሞች ከነግዛቶቻቸው ያዙ።

19. እግዚአብሔር ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፤ ስለዚህ ኰረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለ ነበሯቸው ከዚያ አሳደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም።

20. ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች፤ እርሱም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች ከውስጧ አሳደደ።

21. የብንያም ልጆች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ከዚያ ሊያስወጧቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያቡሳውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከብንያማውያንጋር በዚያ አብረው ይኖራሉ።

22. የዮሴፍ ወገን ደግሞ ቤቴልን ወጉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበር።

23. እነርሱም ቀደም ሲል ሎዛ ትባል ወደ ነበረችው ወደ ቤቴል ሰላዮችን በላኩ ጊዜ፣

24. ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማዪቱ ሲወጣ አይተው፤ “የከተማዪቱን መግቢያ አሳየን፤ እኛም ምሕረት እናደርግልሃለን” አሉት።

25. እርሱም አሳያቸው፤ እነርሱም ከሰውየውና ከቤተ ሰቡ በስተቀር የከተማዪቱን ሕዝብ በሰይፍ ስለት ፈጁ።

26. ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራ፤ ስሟንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራው በዚሁ ስም ነው።

27. የምናሴ ነገድ ግን በቤትሳን፣ በታዕናክ፣ በዶር፣ በይብለዓም፣ በመጊዶንና በየአካባ ቢያቸው ያሉት መንደሮች ነዋሪውን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ ከነዓናውያን ኑሮአቸውን በዚያው ለማድረግ ወሰኑ።

28. እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጒልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ፈጽሞ አላስወጧቸውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 1