ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 1:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ይሁዳ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ላይ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ ቤዜቅ በተባለውም ስፍራ ዐሥር ሺህ ሰው ገደሉ።

5. በዚህም ኦዶኒቤዜቅን አግኝተው ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን ድል አደረጉ።

6. አዶኒቤዜቅም ከዚያ ሸሸ፤ እነርሱ ግን አሳደው ያዙት፤ የእጆቹንና የእግሮቹንም አውራ ጣቶች ቈረጡ።

7. ከዚያም አዶኒቤዜቅ፣ “የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር የወደቀ ፍርፋሪ ይለቃቅሙ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የፈጸምሁትን አመጣብኝ” አለ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ በዚያም ሞተ።

8. የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ወግተው ያዟት፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት መተው፣ በእሳት አቃጠሏት።

9. ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሰዎች በኰረብታማው አገር፣ በኔጌብና በምዕራቡ ኮረብታ ግርጌ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ወረዱ፤

10. ቀደም ሲል ቂርያት አርባቅ ተብላ በምትጠራው በኬብሮን በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ድል አደረጉ።

11. ከዚያም ቀደም ሲል ቅርያትሤፍር ተብላ በምትጠራው በዳቤር በሚኖሩት ሰዎች ላይ ዘመቱ።

12. ካሌብም፣ “ቅርያት ሤፍርን ወግቶ ለሚይዛት ሰው ልጄን ዓክሳንን እድርለታለሁ” አለ።

13. በዚህ ጊዜ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዘ፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳንን ዳረለት።

14. እርሷም ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜ፣ አባቷ የዕርሻ መሬት እንዲሰጠው ይለምነው ዘንድ አጥብቃ ነገረችው፤ ካሌብም እርሷ ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

15. እርሷም፣ “እባክህ አንድ ነገር አድርግልኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 1