ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 8:11-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. በእነዚህም ፊት ከእስራኤል ቤት ሰባ ሽማግሌዎች ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆሞ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም በእጃቸው ጥና ይዘዋል፤ መልካም መዐዛ ያለው የዕጣን ጢስም እየተትጐለጐለ ይወጣ ነበር።

12. እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች እያንዳንዳቸው በጣዖታቸው ምስል ጓዳ ውስጥ በጨለማ የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱ፣ ‘እግዚአብሔር አያየንም፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአል” ይላሉ” አለኝ።

13. ደግሞም፣ “ከእነዚህ የባሰ አስጸያፊ ነገር ሲሠሩ ታያለህ” አለኝ።

14. ከዚህም በኋላ በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር መግቢያ አመጣኝ፤ በዚያም ሴቶች ተቀምጠው ተሙዝ ለተባለው ጣዖት ሲያለቅሱ አየሁ።

15. እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን አይተሃልን? ከዚህም የባሰ አስጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።

16. ደግሞም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ እነሆም በመተላለፊያውና በመሠዊያው መካከል በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ ሃያ አምስት ሰዎች ያህል ነበሩ፤ ጀርባቸውን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አድርገው ለምትወጣዋ ፀሓይ ይሰግዱ ነበር።

17. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን አይተሃልን? የይሁዳ ቤት በዚህ ቦታ የሚፈጽሙት ጸያፍ ተግባር ቀላል ነገር ነውን? ምድሪቱንስ በዐመፅ በመሙላት ዘወትር ያስቈጡኝ ዘንድ ይገባልን? እነሆ፤ ቅርንጫፉን ወደ አፍንጫቸው አቅርበዋል!

18. ስለዚህ በቍጣ እመጣባቸዋለሁ፤ በርኅራኄ ዐይን አላያቸውም፤ ከሚመጣባቸው ነገር አላድናቸውም፤ ወደ ጆሮዬም ቢጮኹ አልሰማቸውም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 8