ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 7:10-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “ ‘እነሆ ቀኑ ይኸው ደረሰ! የጥፋት ፍርድ ተገልጦአል፤ በትሩ አቈጥቍጦአል፤ ትዕቢት አብቦአል።

11. ዐመፅ አድጋ የክፋት በትር ሆነች፤ ከሕዝቡ አንድም አይተርፍም፤ ከሰዎቹ፣ ከሀብታቸውና እርባና ካለው ነገር አንዳች አይቀርም።

12. ጊዜው ደርሶአል፤ ቀኑም ይኸው! መዓት በሕዝቡ ሁሉ ላይ ስለ መጣ፣ የሚገዛ አይደሰት፤ የሚሸጥም አይዘን።

13. ሁለቱ በሕይወት እስካሉ ድረስ ሻጩ የሸጠውን መሬት አያስመልስም፤ ስለ መላው ሕዝብ የተነገረው ራእይ አይለወጥምና። ከኀጢአታቸው የተነሣ ሕይወቱን ማትረፍ የሚችል አንድም አይገኝም።

14. መለከት ቢነፉም፣ ሁሉንም ነገር ቢያዘጋጁም፣ ወደ ጦርነት የሚሄድ አንድ እንኳ አይኖርም፤ መዓቴ በሕዝብ ሁሉ ላይ መጥቶአልና።

15. “በውጭ ሰይፍ፣ በውስጥ ደግሞ ቸነፈርና ራብ አለ፤ በገጠር ያሉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በከተማ ያሉትም በራብና በቸነፈር ያልቃሉ።

16. ተርፈው ያመለጡት ሁሉ በሸለቆ እንደሚኖሩ ርግቦች ስለ ኀጢአታቸው እያለቀሱ በተራራ ላይ ይሆናሉ።

17. እጅ ሁሉ ይዝላል፤ ጒልበት ሁሉ ውሃ ይሆናል።

18. ማቅ ይለብሳሉ፤ ሽብርም ይውጣቸዋል። ፊታቸው ኀፍረት ይለብሳል፤ ራሳቸውም ይላጫል።

19. ብራቸውን በየጐዳናው ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም እንደ ርኵስ ነገር ይቈጠራል። በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ በኀጢአት እንዲወድቁ ዕንቅፋት ሆኖባቸዋልና በልተው አይጠግቡበትም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉበትም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 7