ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 45:14-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ዘይቱ በባዶስ ሲለካ የተወሰነው መስፈሪያ ከእያንዳንዱ ሆመር አንድ ዐሥረኛ ባዶስ ይሆናል፤ ይኸውም ዐሥር ባዶስ ወይም አንድ ሆመር ነው፤ ዐሥር ባዶስ ከአንድ ሆመር ጋር እኩል ነውና።

15. እንዲሁም ውሃ ከጠገበው ከእስራኤል መሰማሪያ፣ ሁለት መቶ በግ ካለው ከእያንዳንዱ መንጋ አንድ በግ ይውሰድ። ይህ ሁሉ ለሕዝቡ ማስተስረያ ለሚሆነው ለእህል ቍርባን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለኅብረት መሥዋዕት ይውላል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

16. የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይህን ልዩ መባ ለእስራኤል ገዥ ይሰጣሉ።

17. በበዓላት፣ በወር መባቻና በሰንበታት፣ ለእስራኤል ቤት በተወሰኑት በዓላት ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን ማቅረብ የገዡ ኀላፊነት ነው፤ ለእስራኤል ቤት ማስተስረያ እንዲሆንም የኀጢአት መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ያቀርባል።’

18. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ፤ መቅደሱንም አንጻው።

19. ካህኑም ከኀጢአቱ መሥዋዕት ደም በመውሰድ በቤተ መቅደሱ በር መቃኖች፣ በመሠዊያው ላይኛ ዕርከን አራት ማእዘንና በውስጠኛው አደባባይ በር መቃኖች ላይ ይርጨው።

20. አንድ ሰው ሳያስብ ወይም ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፤ ወር በገባ በሰባተኛው ቀን ይህን ታደርጋለህ፤ በዚህ ዐይነት ለቤተ መቅደሱ ታስተሰርያላችሁ።’

21. “ ‘በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታከብራላችሁ፤ ይህም እርሾ የሌለበትን እንጀራ የምትበሉበት ሰባት ቀን የሚከበር በዓል ነው።

22. በዚያም ቀን ገዢው ስለ ራሱና ስለ ምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ አንድ ወይፈን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል።

23. በዓሉ በሚከበርበት በሰባቱ ቀን ገዡ በየዕለቱ እንከን የሌለባቸውን ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ በየዕለቱም ለኀጢአት መሥዋዕት አውራ ፍየል ያቅርብ።

24. ለአንዱ ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ለአንድ አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን አድርጎ፣ ለእያንዳንዱም ኢፍ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት አብሮ ያቅርብ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 45