ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 44:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም ያ ሰው ለምሥራቅ ትይዩ ወደ ሆነው በስተ ውጩ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር መልሶ አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር።

2. እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ይህ በር እንደ ተዘጋ ይኖራል፤ መከፈት የለበትም፤ ማንም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክእግዚአብሔር ገብቶበታልና፤ ተዘግቶ ይኖራል።

3. በእግዚአብሔር ፊት ይበላ ዘንድ በመግቢያው በር ገብቶ ውስጥ ሊቀመጥ የሚችለው ገዡ ራሱ ብቻ ነው፤ በመግቢያው መተላለፊያ በረንዳ እንደ ገባ መውጣትም የሚችለው በዚያው ነው።”

4. ከዚያም ያ ሰው በሰሜኑ በር በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አመጣኝ፤ እኔም ተመለከትሁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞልቶት አየሁ፤ በግንባሬም ተደፋሁ።

5. እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥርዐት የምነግርህን ሁሉ በጥንቃቄ አስተውል፤ በሚገባ አድምጥ፤ ልብም በለው። የቤተ መቅደሱን መግቢያና የመቅደሱን መውጫዎች ሁሉ አስተውል፤

6. ለዐመፀኛው የእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አስጸያፊ ሥራችሁ ከእንግዲህ ያብቃ!

7. ከአስጸያፊ ሥራችሁም ሌላ ምግብ፣ ስብና ደም ስታቀርቡ ልባቸውንና ሥጋቸውን ያልተገረዙትን እንግዶች ወደ መቅደሴ በማስገባት ቤተ መቅደሴን አረከሳችሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አፈረሳችሁ።

8. እናንተ ራሳችሁ ማድረግ የሚገባችሁን ቅዱሳት ሥርዐቶቼን በመፈጸም ፈንታ ባዕዳንን በኀላፊነት በመቅደሴ አስቀመጣችሁ።

9. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ ባዕድ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር ቢሆንም እንኳ ወደ መቅደሴ አይግባ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 44