ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 40:29-49 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. የዘብ ቤቶቹ፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር። መግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳዎቹ በዙሪያቸው መስኮቶች ነበሯቸው። ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

30. በውስጠኛው አደባባይ ዙሪያ ያሉት የመግቢያው በር መተላለፊያ በረንዳዎቹ ርዝመት ሃያ አምስት ክንድ ሲሆን፣ ወርዳቸው ደግሞ አምስት ክንድ ነበር።

31. መተላለፊያ በረንዳው ከውጭው አደባባይ ጋር ትይዩ ነው፤ የዘምባባ ዛፎች በዐምዶቹ ላይ ተቀርጸዋል፤ እስከ መግቢያው ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

32. ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ መግቢያ በሩንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

33. የዘብ ቤቶቹ፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ መግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳው ዙሪያውን መስኮቶች ነበሩት፤ የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

34. መተላለፊያ በረንዳው ከውጩ አደባባይ ትይዩ ነው፤ በዐምዶቹ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል፤ እስከ መግቢያ ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

35. ከዚያም ወደ ሰሜን በር አመጣኝ፤ ለካውም፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

36. የዘብ ቤቶቹ፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦቹና መተላለፊያ በረንዳው መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩት። የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

37. መተላለፊያ በረንዳው ከውጩ አደባባይ ትይዩ ነው፤ በዐምዶቹም ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል፤ እስከ መግቢያው ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

38. በእያንዳንዱ የውስጥ መግቢያ በር መተላለፊያ በረንዳ አጠገብ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚታጠብበት በር ያለው ክፍል አለ።

39. በመግቢያው በር ላይ ባለው መተላለፊያ በረንዳው ሥር በግራና በቀኝ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የኀጢአትና የበደል መሥዋዕት የሚታረዱበት ሁለት ሁለት ጠረጴዛዎች አሉ።

40. ከመግቢያው በር ላይ ባለው መተላለፊያ በረንዳ በስተ ውጭው ግንብ ወደ ሰሜን በር መግቢያ ላይ ባሉት ደረጃዎች አጠገብ ከግራና ከቀኝ ሁለት ሁለት ጠረጴዛዎች ይገኛሉ።

41. ስለዚህ በአንዱ በር በኩል አራት፣ በሌላውም በኩል አራት ጠረጴዛዎች፤ መሥዋዕቱ የሚታረድባቸው በድምሩ ስምንት ጠረጴዛዎች አሉ ማለት ነው።

42. ለሚቃጠለው መሥዋዕት መገልገያ የሆኑ፣ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ጠረጴዛዎች ነበሩ፤ የእያንዳንዳቸው ርዝመት፣ ወርድና ቁመት አንድ ክንድ ተኩል ነበር፤ በእነዚህም ላይ ለሚቃጠለው መሥዋዕትና ለሌላውም መሥዋዕት ማረጃ የሚሆኑ መሣሪያዎች ይቀመጡባቸው ነበር።

43. እንዲሁም አንዳንድ ስንዝር የሚሆኑ ሁለት ጣት ያላቸው ሜንጦዎች በግንቡ ዙሪያ ተንጠልጥለው ነበር፤ ጠረጴዛዎቹም የመሥዋዕቱ ሥጋ ማስቀመጫ ነበሩ።

44. በውስጠኛው አደባባይ፣ ከውስጠኛው በር ውጭ፣ ሁለት ክፍሎች ነበሩ፤ አንዱ በደቡብ ትይዩ በሰሜን በር በኩል ሲሆን፣ ሌላው በሰሜን ትይዩ በደቡብ በር በኩል ነበር።

45. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “በደቡብ ትይዩ ያለው ክፍል በቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚያገለግሉ ካህናት ሲሆን፣

46. በሰሜን ትይዩ ያለው ክፍል ደግሞ በመሠዊያው ላይ ለሚያገለግሉ ካህናት ነው። እነዚህም የሳዶቅ ልጆች ሲሆኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት ቀርበው ማገልገል የሚችሉ ሌዋውያን እነርሱ ብቻ ናቸው።”

47. ከዚያም አደባባዩን ለካው፤ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ፣ ወርዱ መቶ ክንድ እኩል በእኩል ባለ አራት ማእዘን ነበር። መሠዊያውም በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ነበር።

48. ወደ ቤተ መቅደሱም መተላለፊያ በረንዳ አመጣኝ፤ የመተላለፊያ በረንዳዎቹን ዐምዶች ለካ፤ በአንዱ በኩል አምስት ክንድ በሌላውም እንዲሁ አምስት ክንድ ነበር። የመግቢያው በር ርዝመት ዐሥራ አራት ክንድ ሲሆን፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦች ስፋት በአንዱ በኩል ሦስት ክንድ፣ በሌላውም እንዲሁ ሦስት ክንድ ነበሩ።

49. የመተላለፊያው በረንዳ ርዝመት ሃያ ክንድ፣ ከፊት እስከ ኋላ ያለውም ወርድ ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበር። ወደ ቤተ መቅደሱም የሚያደርሱ ዐሥር ደረጃዎች የነበሩ ሲሆን፣ በየዐምዱም ጐንና ጐን ምሰሶዎች ነበሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 40