ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 4:3-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. የብረት ምጣድ ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል እንደ ብረት ቅጥር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ እርሷ አዙር፤ የተከበበች ትሆናለች፤ አንተም ትከባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።

4. “አንተ በግራ ጐንህ ተኛ፤ የእስራኤልም ቤት ኀጢአት በአንተ ላይ ይሁን፤ በዚህ ጐንህ በተኛህበት ቀን ቊጥር ኀጢአታቸውን ትሸከማለህ።

5. እነርሱ ኀጢአት ባደረጉባቸው ዓመታት መጠን የቀን ቊጥር መድቤብሃለሁ። ስለዚህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን የእስራኤልን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ።

6. “ይህን ከፈጸምህ በኋላ ደግሞ በቀኝ ጐንህ ተኝተህ የይሁዳን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ፤ ለእያንዳንዱ ዓመት አንድ አንድ ቀን በማድረግ አርባ ቀን መድቤብሃለሁ።

7. ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ታዞራለህ፣ በራቍት ክንድህ ትንቢት ተናገርባት።

8. የከበባህን ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከአንዱ ጐን ወደ ሌላው መገላበጥ እንዳትችል በገመድ አስርሃለሁ።

9. “ስንዴና ገብስ፣ ባቄላና ምስር እንዲሁም ዘንጋዳና ጠመዥ ወስደህ በአንድ ሸክላ ውስጥ አስቀምጥ፤ ከዚያም ለራስህ እንጀራ ጋግር፤ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን በጐንህ በምትተኛበት ጊዜ ትመገበዋለህ።

10. በየቀኑ የምትበላውን እህል ሃያ ሃያ ሰቅል መዝነህ አስቀምጥ፤ በተወሰነ ጊዜ ትበላዋለህ፤

11. የምትጠጣውንም ውሃ አንድ ስድስተኛ ኢን ለክተህ አስቀምጥ፤ በተወሰነ ጊዜ ትጠጣዋለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 4