ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 4:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ የሸክላ ጡብ ወስደህ ከፊት ለፊትህ አስቀምጥ፤ የኢየሩሳሌምን ከተማ ካርታ ሥራበት።

2. ከዚያም በወታደር እንደሚከበብ ክበባት፤ ምሽግ ሥራባት፤ ዐፈር ደልድልባት፤ ጦር ሰፈሮችን ቀብቅብባት፤ ቅጥር መደርመሻ ግንዶችንም በዙሪያዋ አስቀምጥባት።

3. የብረት ምጣድ ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል እንደ ብረት ቅጥር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ እርሷ አዙር፤ የተከበበች ትሆናለች፤ አንተም ትከባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።

4. “አንተ በግራ ጐንህ ተኛ፤ የእስራኤልም ቤት ኀጢአት በአንተ ላይ ይሁን፤ በዚህ ጐንህ በተኛህበት ቀን ቊጥር ኀጢአታቸውን ትሸከማለህ።

5. እነርሱ ኀጢአት ባደረጉባቸው ዓመታት መጠን የቀን ቊጥር መድቤብሃለሁ። ስለዚህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን የእስራኤልን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ።

6. “ይህን ከፈጸምህ በኋላ ደግሞ በቀኝ ጐንህ ተኝተህ የይሁዳን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ፤ ለእያንዳንዱ ዓመት አንድ አንድ ቀን በማድረግ አርባ ቀን መድቤብሃለሁ።

7. ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ታዞራለህ፣ በራቍት ክንድህ ትንቢት ተናገርባት።

8. የከበባህን ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከአንዱ ጐን ወደ ሌላው መገላበጥ እንዳትችል በገመድ አስርሃለሁ።

9. “ስንዴና ገብስ፣ ባቄላና ምስር እንዲሁም ዘንጋዳና ጠመዥ ወስደህ በአንድ ሸክላ ውስጥ አስቀምጥ፤ ከዚያም ለራስህ እንጀራ ጋግር፤ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን በጐንህ በምትተኛበት ጊዜ ትመገበዋለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 4