ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 39:2-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፤ እንዲሁም እጐትትሃለሁ፤ ከሩቅ ሰሜን አምጥቼ በእስራኤል ተራሮች ላይ እሰድሃለሁ።

3. በግራ እጅህ ያለውን ቀስትህን እመታለሁ፤ በቀኝ እጅህ የያዝሃቸውንም ፍላጾች አስረግፍሃለሁ።

4. አንተና ወታደሮችህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝቦች በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ። ነጣቂ አሞሮችና የዱር አራዊት ይበሏችሁ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ።

5. አውላላ ሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

6. በማጎግና ያለ ሥጋት በባሕር ዳርቻ በሚኖሩት ላይ እሳት እሰዳለሁ፤ እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”

7. “ ‘ቅዱሱ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል ዘንድ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቅዱስ ስሜ እንዲናቅ፣ እንዲቃለል አልፈልግም፤ አሕዛብም እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

8. እነሆ ይመጣል፤ በእርግጥም ይሆናል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያ ያልሁት ቀን ይህ ነው።

9. “ ‘ከዚያም በእስራኤል ከተሞች የሚኖሩ ሁሉ ወጥተው የጦር መሣሪያውን፣ ትልልቁንና ትንንሹን ጋሻ፣ ቀስቱን፣ ፍላጻውን፣ የጦር ዱላውንና ጦሩን ሰብስበው ማገዶ በማድረግ ያነዱታል፤ ሰባት ዓመት ይማግዱታል።

10. ከሜዳ ላይ ዕንጨት መልቀም፣ ከዱርም ዛፍ መቍረጥ አያስፈልጋቸውም፤ የጦር መሣሪያቸውን በመማገድ ይጠቀማሉና። የዘረፏቸውን ይዘርፋሉ፤ የበዘበዟቸውን ይበዘብዛሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

11. “ ‘በዚያ ቀን ሰዎች በምሥራቅ በኩል ወደ ባሕሩ በሚጓዙበት ሸለቆ፣ ለጎግ የመቃብር ስፍራ በእስራኤል እሰጠዋለሁ። ጎግና ሰራዊቱ ሁሉ በዚያ ስለሚቀበሩ፣ የተጓዦችን መንገድ ይዘጋሉ፤ ስለዚህም የሐሞን ጎግ ሸለቆ ይባላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 39