ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 39:11-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “ ‘በዚያ ቀን ሰዎች በምሥራቅ በኩል ወደ ባሕሩ በሚጓዙበት ሸለቆ፣ ለጎግ የመቃብር ስፍራ በእስራኤል እሰጠዋለሁ። ጎግና ሰራዊቱ ሁሉ በዚያ ስለሚቀበሩ፣ የተጓዦችን መንገድ ይዘጋሉ፤ ስለዚህም የሐሞን ጎግ ሸለቆ ይባላል።

12. “ ‘ምድሪቱን ለማጽዳት፣ የእስራኤል ቤት ሰዎች ሰባት ወር ሙሉ ይቀብሯቸዋል።

13. የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ይቀብሯቸዋል፤ እኔ የምከብርበትም ዕለት የመታሰቢያ ቀን ይሆናቸዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

14. “ ‘ሰዎች ምድሪቱን ለማጽዳት በየጊዜው ይቀጠራሉ። አንዳንዶቹ ምድሪቱን ያስሳሉ፤ ከእነርሱም በተጨማሪ ሌሎች ሳይቀበሩ የቀሩትን ይቀብራሉ። ከሰባት ወር በኋላም ፍለጋ ይጀምራሉ።

15. እነርሱም በምድሪቱ መካከል ሲሄዱ፣ ከእነርሱ አንዱ የሰው ዐፅም ባየ ቍጥር ምልክት ያደርግበታል፤ ይህም መቃብር ቈፋሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ነው።

16. በዚያም ሐሞና የምትባል ከተማ አለች፤ ስለዚህ ምድሯን ያጸዳሉ።’

17. “ ‘የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማንኛውንም ዐይነት ወፍና የዱር አራዊት ሁሉ ጥራ፤ እንዲህም በላቸው፤ “ከየአቅጣጫው ተሰብስባችሁ እኔ ወደማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት ኑ፤ ይህም በእስራኤል ተራሮች ላይ የሚሆን ታላቁ መሥዋዕት ነው። በዚያ ሥጋ ትበላላችሁ፤ ደምም ትጠጣላችሁ።

18. እንደ አውራ በግና እንደ ጠቦት፤ እንደ ፍየልና እንደ ወይፈን፣ የኀያላን ሰዎችን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድርንም መሳፍንት ደም ትጠጣላችሁ፤ እነዚህ ሁሉ የሰቡ የባሳን ከብቶች ናቸው።

19. እኔ በማዘጋጅላችሁም መሥዋዕት እስክትጠግቡ ስብ ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ደም ትጠጣላችሁ።

20. በገበታዬም ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፣ ኀያላን ሰዎችንና ከየወገኑ የሆኑትን ወታደሮች እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

21. “ክብሬን በአሕዛብ መካከል እገልጣለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ በእነርሱ ላይ ያመጣሁትን ቅጣትና በላያቸው ላይ የጫንሁትን እጅ ያያሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 39