ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 37:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ከዚያም እናንተ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን ከፍቼ ሳወጣችሁ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

14. መንፈሴን በውስጣችሁ አስቀምጣለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤ በገዛ ምድራችሁ አስቀምጣችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ፣ እንዳደረግሁትም ታውቃላችሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።” ’

15. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

16. “የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ በትር ወስደህ፣ ‘የይሁዳና የተባባሪዎቹ የእስራኤላውያን’ ብለህ ጻፍበት። ከዚያም ሌላ በትር ወስደህ፣ ‘የኤፍሬም፣ የዮሴፍና የተባባሪዎቹ የእስራኤል ቤት ሁሉ’ ብለህ ጻፍበት።

17. እንደ አንድ በትር ይሆኑ ዘንድ በእጅህ ላይ አጋጥመህ ያዛቸው።

18. “የአገርህ ልጆች፣ ‘ይህስ ምን ማለትህ እንደሆነ አትነግረንምን?’ ብለው ሲጠይቁህ፣

19. እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትርና የተባባሪዎቹን የእስራኤላውያንን ነገድ በትር እወስዳለሁ፤ ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥሜ አንድ ወጥ በትር አደርጋቸዋለሁ፤ እነርሱም በእጄ አንድ በትር ይሆናሉ።’ ”

20. የጻፍህባቸውን በትሮች ከፊት ለፊታቸው ያዝ፤

21. እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው አሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየስፍራው ሰብስቤ ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።

22. በምድሪቱ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፤ በሁሉም ላይ አንድ ንጉሥ ይነግሣል፤ ከእንግዲህም ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፤ መንግሥታቸውም ከሁለት አይከፈልም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 37