ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 34:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ስለዚህ እረኞች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

10. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በእረኞች ላይ ተነሥቻለሁ፤ ስለ መንጋዬ እጠይቃቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ እረኞች ራሳቸውን መመገብ እንዳይችሉ፣ መንጋዬን እንዳያሰማሩ አደርጋለሁ። መንጋዬን ከአፋቸው አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህም ምግብ አይሆናቸውም።

11. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋቸዋለሁ፤ እጠብቃቸዋለሁም።

12. እረኛ ከመንጋው ጋር ሳለ፣ የተበተኑበትን በጎች እንደሚፈልግ ሁሉ፣ እኔም በጎቼን እፈልጋለሁ። በደመናና በጨለማቀን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ።

13. ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።

14. በመልካሙ ስፍራ አሰማራቸዋለሁ፤ የእስራኤል ተራሮች ከፍታም የግጦሽ መሬት ይሆናቸዋል። በመልካሙ ግጦሽ መሬት ላይ ይተኛሉ፤ እዚያም በእስራኤል ተራሮች ለምለም መስክ ላይ ይመገባሉ።

15. እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፤ አስመስጋቸዋለሁም። ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

16. የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን ግን አጠፋለሁ። መንጋውን በፍትሕ እጠብቃለሁ።

17. “ ‘መንጋዬ ስለ ሆናችሁት ስለ እናንተ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በበግና በበግ መካከል፣ በአውራ በግና በአውራ ፍየል መካከል እፈርዳለሁ።

18. በለምለሙ መስክ ላይ መመገቡ አይበቃችሁምን? የተረፈውን መሰማሪያችሁን ደግሞ በእግራችሁ መረጋገጥ ይገባችኋልን? ንጹሕ ውሃ መጠጣቱ አይበቃችሁምን? የተረፈውንስ በእግራችሁ ማደፍረስ ይገባችኋልን?

19. መንጋዬ የረጋገጣችሁትን መመገብና በእግራችሁ ያደፈረሳችሁትን መጠጣት ይገባዋልን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 34