ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 27:26-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ቀዛፊዎችሽ፣ወደ ጥልቁ ባሕር ይወስዱሻል፤የምሥራቁ ነፋስ ግን፣በባሕሩ መካከል ይሰባብርሻል።

27. የመርከብ አደጋ በሚደርስበሽ ቀን፣ሀብትሽ፣ ሸቀጥሽና የንግድ ዕቃሽ፣መርከብ ነጂዎችሽ፣ መርከበኞችሽና መርከብ ሠሪዎችሽ፣ነጋዴዎችሽና ወታደሮችሽ ሁሉ፣በመርከብ ላይ ያሉትም ሁሉ፣ወደ ባሕሩ ወለል ይዘቅጣሉ።

28. መርከበኞችሽ ሲጮኹ፣የባሕሩ ጠረፍ ይናወጣል።

29. ቀዛፊዎች ሁሉ፣መርከባቸውን ጥለው ይሄዳሉ፤መርከብ ነጂዎችና መርከበኞችም ሁሉ፣ወርደው ባሕሩ ዳር ይቆማሉ፤

30. ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣በምሬት ያለቅሱልሻል፤በራሳቸውም ላይ ዐቧራ ነስንሰው፣በዐመድ ላይ ይንከባለላሉ።

31. ስለ አንቺ ጠጒራቸውን ይላጫሉ፤ማቅም ይለብሳሉ፤በነፍስ ምሬት፣በመራራም ሐዘን ያለቅሱልሻል።

32. ስለ አንቺ በዋይታ ያለቅሳሉ፤እንዲህም እያሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤“ባሕር ውጦት የቀረ፣እንደ ጢሮስ ማን አለ?”

33. ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ፤ብዙ ሕዝቦችን ታጠግቢ ነበር፣በታላቅ ሀብትሽና ሸቀጥሽ፣የምድርን ነገሥታት ታበለጽጊ ነበር።

34. አሁን ግን በጥልቅ ውሃ ውስጥ፣በባሕር ተንኰታኵተሻል፤ጭነትሽና ተሳፋሪዎችሽ ሁሉ፣ከአንቺ ጋር ሰጥመዋል።

35. በጠረፍ አገር የሚኖሩ ሁሉ፣በአንቺ ሁኔታ ተደናገጡ፤ንጉሦቻቸው በፍርሀት ራዱ፤ፊታቸውም ተለዋወጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 27