ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 27:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “ ‘የፋርስ፣ የሉድና የፉጥ ሰዎች፣ወታደር ሆነው በሰራዊትሽ ውስጥአገለገሉ፤ሞገስም ይሆኑሽ ዘንድ፣ጋሻቸውንና የራስ ቍራቸውን በግድግዳሽ ላይ ሰቀሉ።

11. የአራድና የሔሌክ ሰዎች፣ቅጥርሽን በየአቅጣጫው ጠበቁ፤የገማድ ሰዎችም፣ በምሽግሽ ውስጥ ነበሩ።ጋሻቸውንም በቅጥርሽ ዙሪያ ሰቀሉ፤ውበትሽንም ፍጹም አደረጉ።

12. “ ‘ከሀብትሽ ብዛት የተነሣ፣ ተርሴስ ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ታደርግ ነበር፤ ብርና ብረት፣ ቈርቈሮና እርሳስ አምጥታ ሸቀጥሽን ትለውጥ ነበር።

13. “ ‘ያዋን፣ ቶቤልና ሞሳሕ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር፤ ባሪያዎችንና የናስ ዕቃዎችን በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።

14. “ ‘የቤት ቴርጋማ ሰዎችም መጋዣዎችን፣ የጦር ፈረሶችንና በቅሎዎችን በሸቀጥሽ ለወጡ።

15. “ ‘የድዳን ሰዎች ከአንቺ ጋር ተገበያዩ፤ብዙ የጠረፍ አገሮችም የንግድ ደንበኞችሽ ነበሩ፤ በዝኆን ጥርስና በዞጲ ሸቀጥሽን ይገዙ ነበር።

16. “ ‘ምርትሽ ብዙ እንደ መሆኑ፣ ሶርያ ከአንቺ ጋር ትገበያይ ነበር፤ ሸቀጥሽንም በበሉር፣ በሐምራዊ ጨርቅ፣ በወርቀ ዘቦ፣ በጥሩ በፍታ፣ በዛጐልና በቀይ ዕንቍ ይለውጡ ነበር።

17. “ ‘ይሁዳና እስራኤል እንኳ ከአንቺ ጋር ተገበያይተዋል፤ የሚኒትን ስንዴ፣ ጣፋጭ ቂጣ፣ ማር፣ ዘይትና በለሳን በማምጣት በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።

18. “ ‘ከሀብት ከንብረትሽ ብዛት የተነሣ፣ ደማስቆ የኬልቦንን የወይን ጠጅና፣ የዛሐርን የበግ ጠጒር በማቅረብ ከአንቺ ጋር ተገበያ ይታለች።

19. “ ‘ዌንዳንና ያዋን ከኦሴል መጥተው ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር፤ ቀልጦ የተሠራ ብረትን፣ ብርጒድንና ቀረፋን በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።

20. “ ‘ድዳን ግላስ በማቅረብ ከአንቺ ጋር ትነግድ ነበር።

21. “ ‘የዐረብና የቄዳር መሳፍንት ሁሉ ደምበኞችሽ ነበሩ፤ ጠቦትና አውራ በግ፣ ፍየልም አምጥተው ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 27