ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 27:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ጢሮስ ሙሾ አውርድ፤

3. በባሕር መግቢያ ላይ ለምትገኘውና በብዙ ጠረፎች ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር ለምትነግደው ለጢሮስ እንዲህ በላት፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ጢሮስ ሆይ!፤“ፍጹም ውብ ነኝ” ብለሻል፤

4. ዳርቻሽ በባሕር መካከል ነው፤ሠሪዎችሽም ፍጹም ውብ አድርገውሻል።

5. ሳንቃዎችሽን ሁሉ፣ከሳኔር በመጣ ጥድ ሠሩ፤ደቀልንም ይሠሩልሽ ዘንድ፤ከሊባኖስ ዝግባ አመጡ።

6. ከባሳን በመጣ ወርካ፣መቅዘፊያሽን ሠሩ፤ከቆጵሮስ ጠረፍ በመጣ ዝግባ፣በዝኆን ጥርስ ለብጠው ወለልሽን ሠሩ።

7. የመርከቦችሽ ሸራ ጥልፍ ሥራ ያለበት የግብፅ በፍታ ነበረ፤ይህም እንደ ዐርማ አገለገለሽ።መጋረጃዎችሽ ከኤሊሳ ጠረፍ የመጡ፣ባለ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀለም ነበሩ።

8. ቀዛፊዎችሽ ከሲዶናና ከአራድ የመጡ ነበሩ፤ጢሮስ ሆይ፤ የራስሽ ጠቢባን የመርከቦችሽ መሪዎች ነበሩ።

9. ልምድ ያካበቱ የጌባል ባለ ሙያዎች፣መርከብሽን ለመገጣጠም በመካከልሽ ነበሩ፤የባሕር መርከቦችና መርከበኞቻቸው ሁሉ፣ከአንቺ ጋር ሊገበያዩ ይመጡ ነበር።

10. “ ‘የፋርስ፣ የሉድና የፉጥ ሰዎች፣ወታደር ሆነው በሰራዊትሽ ውስጥአገለገሉ፤ሞገስም ይሆኑሽ ዘንድ፣ጋሻቸውንና የራስ ቍራቸውን በግድግዳሽ ላይ ሰቀሉ።

11. የአራድና የሔሌክ ሰዎች፣ቅጥርሽን በየአቅጣጫው ጠበቁ፤የገማድ ሰዎችም፣ በምሽግሽ ውስጥ ነበሩ።ጋሻቸውንም በቅጥርሽ ዙሪያ ሰቀሉ፤ውበትሽንም ፍጹም አደረጉ።

12. “ ‘ከሀብትሽ ብዛት የተነሣ፣ ተርሴስ ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ታደርግ ነበር፤ ብርና ብረት፣ ቈርቈሮና እርሳስ አምጥታ ሸቀጥሽን ትለውጥ ነበር።

13. “ ‘ያዋን፣ ቶቤልና ሞሳሕ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር፤ ባሪያዎችንና የናስ ዕቃዎችን በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።

14. “ ‘የቤት ቴርጋማ ሰዎችም መጋዣዎችን፣ የጦር ፈረሶችንና በቅሎዎችን በሸቀጥሽ ለወጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 27